በዓሉ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በኢትዮጵያዊ አብሮነት በመከበሩ ተደስተናል- ዳያስፖራዎች

132

ጎንደር ፣ ጥር 12/ 2014(ኢዜአ)  በጎንደር ከተማ የጥምቀት በዓል ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ በኢትዮጵያዊ አብሮነት በመከበሩ ተደስተናል ሲሉ ዳያስፖራዎች ገለጹ።

ዳያስፖራዎቹ በተለያዩ የአገልግሎት መስጫዎች መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው ለኢዜአ አስታውቀዋል።

ከኦስትሪያ ቬና መጥተው በበዓሉ ላይ የታደሙት ወይዘሮ ሳራ ከነአን እንዳሉት በዓለም ላይ እንደ ጥምቀት ያለ በርካታ ሰዎች በነቂስ ወጥተው በተገኙበት በአደባባይ የሚከበር በዓል የለም።

በጎንደር የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቱ ባሻገር ባህላዊ ክዋኔው ጥንታዊ ይዘቱን አለመልቀቁና ኢትዮጵያዊያን ከያሉበት ተሰባስበው በአብሮነት በማክበራቸው የተለየ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

"የህብረተሰቡ አለባበስ፣ የፀጉር አሰራር፣ ሴቶች ለጌጥ የሚጠቀሟቸው ቁሶች፣ የወንዶችና የሴቶች ባህላዊ ጭፈራና ሌሎች ክዋኔዎች ጥንታዊ ይዘታቸውን የጠበቁና አስደሳች ናቸው" ብለዋል።

ወይዘሮ ሳራ እንዳሉት የሆቴሎችና ሌሎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ለዳያስፖራው ማህበረሰብ እያሳዩ ያለው መልካም አቀባበልና መስተንግዶ የተለየ በመሆኑ መጠናከር አለበት።

ከአሜሪካን አገር ሲያትል የመጡት አቶ ያየህይራድ ዮሐንስ በበኩላቸው የጥምቀት በዓል አከባበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ ይዘቱን ጠብቆ በመከበሩ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አንዳንድ የውጭ መንግስታት በአገራችን ባደረሱት ጫና የውጭ መገናኛ ብዙሀን በተከታታይ አሉታዊ ዘገባ ሲያሰራጩ እንደነበር አስታውሰው፣ "በዓሉን ከያለንበት ተሰባስበን በሰላም ማክበራችን ዛሬም የኢትዮጵያን አሸናፊነት ያሳያል" ብለዋል።  

የአንዳንድ የውጭ መገናኛ ብዙሀን  አሉታዊ ዘገባ ለመመከት ዳያስፖራው በሚኖርበት አካባቢ ተሰባስቦ የሚመክት ስራ በመስራቱ ውጤት እየተገኘ መምጣቱን አስታውሰዋል።

የመንግስትን ጥሪ ተቀብለን ከውጭ አገር የመጣነው በአገራችን የተሻለ ሰላምና መረጋጋት እየታየ ስለመሆኑ በማሳየት አሉታዊ እይታን ለማክሸፍ ነው" ሲሉም አክለዋል።

ከዋሽንግተን ዲሲ የመጡት ወይዘሮ ሳባ ማሞ በበኩላቸው "በጎንደር ቤተሰቦች ቢኖሩኝም እስከዛሬ መጥቼ በበዓሉ ላይ ባለመታደሜ ጸጸት አሳድሮብኛል" ሲሉ ገልጸዋል።

በየደረሱበት በተደረገላቸው መልካም አቀባበል ደስተኛ መሆናቸውን የተናገሩት ወይዘሮ ሳባ፣ ወደ ጎንደር ሲመጡ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል።

በጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ባዩት ነገር ሁሉ ከመደነቅ ባለፈ በቀጣይ በየዓመቱ መጥተው በበዓሉ የመታደም ፍላጎት እንዳደረባቸው ነው የተናገሩት።

አስተያየት ሰጪዎቹ ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሯዊና ባህላዊ እሴቶች ለዓለም በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ዘርፍ እንድትጠቀም መንግስት ለዘርፉ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አመልክተዋል ።

ዳያስፖራውም የሀገሪቱን መልካም ገጽታና እሴቶች በማስተዋወቅ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

ዘንድሮ በጎንደር በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ በርካታ ዳያስፖራዎችና የአገር ውስጥ ጎብኚዎች መታደማቸው ተመላክቷል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም