በዓላት በሰላም መከበራቸው የክልሉን ቱሪዝምና ኢኮኖሚ ያነቃቃል

168

ጥር 12/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የተከበሩት የከተራ፣ የጥምቀትና የገና በዓላት በሰላም መጠናቀቁ የክልሉን የቱሪዝም ዘርፍና ኢኮኖሚው ለማነቃቃት የጎላ ፋይዳ አለው ሲል የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው የጥምቀት፣ የከተራና ቀደም ሲል በላልይበላ የተከበረው የገና በዓል በሰላም እንዲጠናቀቅ አስተዋፅኦ ላበረከቱ ለፀጥታ አካላት፣ ወጣቶችና ህዝቡ በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርቧል።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ካለፉት አስቸጋሪ ጊዜያት በመውጣት ሃይማኖታዊና የህዝብ በዓላት በሰላም መከበራቸው ህዝቡ ሁሌም ሰላም ወዳድ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው።

ባለፉት ወራት የፀጥታ አካላትና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ አሸባሪውን ህወሓት ለመመከት በሰሩት ሥራ ዲያስፖራው በየትኛውም አካባቢ ያለስጋት እንዲንቀሳቀስና እንዲጎበኝ ያስቻለ መሆኑን አስታውሰዋል።

የሽብር ቡድኑ በዓሉን ለማደፍረስ የጣረ ቢሆንም በተቀናጀ መንገድ በተሰራ ስራ ሴራውን ማክሸፍ መቻሉን አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

አቶ ግዛቸው እንዳሉት በክልሉ በድምቀት የተከበሩት የገና፣ የከተራና የጥምቀት በዓላት በሰላም መጠናቀቅ የቱሪዝም ዘርፉንና ኢኮኖሚውን ዳግም እንዲነቃቃ የሚያደርግ ነው።በዓላቱ በሰላም መከበር አብሮነትን ከማጠናከርና ኢትዮጵያ ዳግም እንድታሸንፍ ከማድረጉ በተጨማሪ በክልሉ ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች መተማመን የፈጠረ መልካም እድል መሆኑን ተናግረዋል።

“ሃይማኖታዊና ህዝባዊ በዓላቱ የክልሉ ከፍተኛ አመራር ከዲያስፖራውና ከህዝቡ ጋር በኢንቨስትመንትና በችግሮች አፈታት ላይ ተወያይቶ የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያስቀምጥ እድል ፈጥሯል” ሲሉም ተናግረዋል።በሌላ በኩል የክፋት ቡድኖችን ያሳፈረ መሆኑን አመልክተዋል።

በነገው እለት የግዮን በዓል በምዕራብ ጎጃም “ሰክላ” ላይ፤ የአገው ፈረሰኞች ማህበርም በቀጣይ የሚከበሩ በመሆኑ ዲያስፖራው በበዓላቱ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

የጥምቀት፣ የከተራና በላልይበላ ቀደም ሲል የተከበረው የገና በአላት በሰላም እንዲጠናቀቁ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የፀጥታ አካላት፣ ወጣቶችና ህዝቡ አቶ ግዛቸው በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።