የድሬዳዋ ጤና ቢሮ ለሶስት የአፋር ክልል ጤና ጣቢያዎች የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

91

ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ በአፋር ክልል አሸባሪው ህውሃት ወረራ በፈጸመበት ወቅት ያወደማቸውን ሶስት ጤና ጣቢያዎች ስራ ለማስጀመር የሚያግዝ በ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የተገዙ መድኃኒቶች ድጋፍ አደረገ፤

የአስተዳደሩ ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ ጨምሮ የህክምና ባለሙያዎች ያካተተ ቡድን ድጋፉን ለአፋር ክልል ለማስረከብና ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዛሬ ጉዞ ጀምሯል።

ለቡድኑ ሽኝት ያደረጉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ በአፋርና በአማራ ክልሎች የወደሙ የጤና ተቋማት መልሰው ስራ እንዲጀምሩ ለሚደረገው ርብርብ አስተዳደሩ ኃላፊነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል።

በአፋር ክልል የወደሙ ሶስት ጤና ጣቢያዎችን ስራ ለማስጀመር የድሬዳዋ ጤና ቢሮና የግል የጤና ተቋማት ያደረጉት የሚበረታታ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

ድጋፉን ለአፋር ክልል ለማድረስ ጉዞ የጀመረው ቡድን አስተባባሪ የድሬዳዋ አስተዳደር ጤና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ለምለም በዛብህ በበኩላቸው ድጋፉ አሸባሪው ቡድን ያወደማቸውን ሶስት የጤና ተቋማት መሠረታዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል ብለዋል።

በመተጋገዝና በአንድነት የጤና መሠረተ ልማትን በመመለስ ጤናው የተጠበቀ ህብረተሰብ የማፍራቱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ድጋፉ የተለያዩ መድኃኒቶች፣ የድንገተኛ ህክምናና የማዋለጃ አገልግሎቶች መስጫ የህክምና ቁሳቁሶች፣ የንፅህናና ሌሎች መሠረታዊ የህክምና መገልገያዎችን ያካተተ ነው።

በተጨማሪም በአፋር ክልል ቆይታ የህክምና ባለሙያዎች ቡድን ሙያዊ ዕገዛ ለማድረግ ማቀዱንም ወይዘሮ ለምለም ገልጸዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር በአፋር ክልል የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም መሰል ድጋፍ ሲያደርግ በአመቱ ይህ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም