የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ በኢትዮጵያ ሰላም መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው

117

ጥር 12/2014/ኢዜአ/ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ በኢትዮጵያ ሰላም መኖሩን የሚያረጋግጥ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

በኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ የተከናወኑ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ እንዳይካሄድ ለማድረግ "ስውር እጆች" እንደነበሩ ገልጸዋል።

በዋናነትም "ሰላም የለም፤ የጸጥታ ሁኔታው አስጊ ነው፤ ኢትዮጵያ ጉባኤውን ማስተናገድ አትችልም፤ የሚሉ ብዙ ጥረቶች ነበሩ" ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለውን ነባራዊ እውነታ በማስረዳት ሴራው እንዲከሽፍ ለማድረግ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችና ግለሰቦች ጋር በመሰራቱ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል አምባሳደር ዲና።

ኢትዮጵያ የህብረቱንም ሆነ ሌሎች ትላልቅ ስብሰባዎችን በስኬት የማካሄድ ልምድ እንዳላት ገልጸው በአዲስ አበባ እንዳይካሄድፍ የተለያዩ መሰናክሎች እንደነበሩ አስታውሰዋል።

በመሆኑም 35ኛው የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው።

ለህብረቱ ጉባኤ ስኬታማ ክንውን እንዲሁም በአጋጣሚው የኢትዮጵያ ገፅታ እንዲገነባ ብሔራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዝግጅት እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ ከካናዳው አቻቸው እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ከኖርዌይ አቻቸው ጋር በሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ስኬታማ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በአረብ ኤምሬቶች ንጹሃን ላይ ባለፈው ሳምንት የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት በማውገዝ ለአገሪቱ መንግስትና ህዝብ የሃዘን መልዕክት መተላለፉንም አስታውሰዋል።

አሸባሪው ህወሓት ወደ ትግራይ ሰብዓዊ እርዳታ ለማድረስ መሰናክል እየፈጠረ መሆኑን መንግስት ለሚመለከታቸው አካላት አሳውቋል ብለዋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ በኢትዮጵያ ላይ የሚያወጡትን የተሳሳተ መረጃና ለሽብር ቡድኑ የሚያደርጉት የመረጃና ሌሎች ድጋፎች አግባብ አለመሆናቸውን ለድርጅቱ የአስተዳደር ቦርድ  ደብዳቤ መጻፉን ጠቁመዋል።

በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት በመምጣት ሲምፖዚየሞችን በማካሄድ፣ በጦርነት የተጎዱ ሥፍራዎችን በመጎብኘት፣ በመልሶ ግንባታ በመሳተፍ፣ እንዲሁም በላልይበላ እና በጎንደር ለበዓላት በመታደም አለኝታነታቸውን በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም