መልከ ብዙው የዓለም ቅርስ ጥምቀት

191

ጥር 12/2014 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዓለም ቅርስነት ያበረከተችው በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው የጥምቀት የአደባባይ ክብረ በዓል መልከ ብዙ ትዕይንቶች አሉት።

ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባለፈ ማህበራዊ መስተጋብሩ፣ ባህላዊ አለባበስና ትውፊታዊ ክዋኔዎቹ ልዩ ለዛ ይሰጡታል።

ጥምቀት በምዕመናኑ ዘንድ በተለይ በወጣቶች በየዓመቱ የሚናፈቅ ማህበራዊ ገጽታዎች አሉት።

በቤተ ክርስቲያኗ የገዳማት አስተዳድር መምሪያ ምክትል ሃላፊ መላከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደጊዮርጊስ ታዬ፤ የጥምቀት የሰው ልጅ የዕዳ ደብዳቤ የተደመሰሰበትና ለክርስቲያኖች ሁለተኛ ልደት ምሳሌ ብሎም የክርስቶስ ጥምቀት መታሰቢያ ስርዓት ነው ይላሉ።

ከጥንት ጀምሮ በየዓመቱ የሚከበረው ጥምቀት ከሃይማኖታዊ እሴቱ ተሻግሮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ የአገር ሃብት ሆኗል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በሌሎች ትምህርት ተቋማት የኤብራይስጥ ቋንቋና የስነ ጥበብ መምህሩ ዶክተር ኢያቄም ፔርሱን፤ ጥምቀት በግብጽ በፖለቲካ ምክንያት መከበር እንዳቆመ ጠቁመው አሁን ላይ በአፍሪካ በኢትዮጵያና ኤርትራ ብቻ እንደሚከበር ገልጸዋል።

በዓሉ የህዝብ አንድነትና ትስስር የሚያሳይ በመሆኑ በኢትዮጵያ እሴቱ ሳይደብዝዝ መከበሩን ቀጥሏል ብለዋል።

የኪነ ጥበብ ባለሙያው ንብረት ገላው፤ ቤተ ክርስቲያኗ ፊደል ቀርጻ፣ ብራና ዳምጣ፣ ዘመን ቀምራ ለአገር ያስረከበችና ለዘመናት ያሻገረች መሆኗን ገልጿል።

የጥምቀት አከባበር ስርዓት የኢትዮጵያዊያን ጥብብ የሚንጸባረቅበት በምስጢርና በጥበብ የሚከወኑ ሁነቶች ከሚታዩበት አደባባይ በዓላት መካከል አንዱ መሆኑንም ተናግሯል።

ቋንቋው፣ የካህናት ልብሰ ተክህኖው፣ ወረቡ፣ ያሬዳዊ ዝማሬው፣ የዜማ መሳሪያዎች ሁለንተናዊ ክዋኔው ሁሉ ሰማያዊ ተውኔት ነው የሚለው አርቲስቱ ጥምቀት ለዘመናት ያልተበረዘ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሀብት መሆኑን አስረድቷል።

በመሆኑም ጥምቀት ከአምልኮ ባሻገር ያለው የአከባበር ክዋኔው በዘመናዊ ትምህርት የማይገኝና በርካታ አይነት አገር በቀል ትዕይንቶች የሚስተናግዱበት በመሆኑ “የጥበብ አቅም ማሳያ ዐውደ ጥበብ ነው” ይላል።

ጥምቀት ከእምነቱ ተከታዮች አምልኮ ባሻገር በኢትዮጵያ ወካይ የዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ የአገር የጋራ ሃብት ሆኗል ነው ያለው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼