“ሠራዊቱ የሚለካው በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሄሩ አይደለም”-ጀነራል አበባው ታደሰ

143

ጥር 12 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የኢትዮጵያ ሠራዊት የሚለካው በስራው ስኬት እና በግዳጅ አፈፃፀሙ እንጂ በብሄሩ አይደለም" ሲሉ የመከላከያ ሰራዊት ምክትል ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጀነራል አበባው ታደሰ ገለጹ።

ከዚህ በፊት በነበረው የብሄር ተኮር የሠራዊት ግንባታ ዋጋ የከፈለው እራሱ ሠራዊቱ ነው ያሉት ጀነራል አበባው ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ እና በሞያው ብቁ የሆነ ሠራዊት እየተገነባ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በቅርቡ የተካሄደው ወታደራዊ የማዕረግ እና የሜዳልያ ሽልማት በግዳጅ አፈፃፀም ላይ የተመሰረተ፣ በየደረጃው ላሉ እዞች ማዕረግ የተሰጠበት፣ የሠራዊቱ አመራሮችን የሚመጥን እና የሠራዊቱን ሞራል የገነባ እንደነበር ገልፀዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ ከአሸባሪው ህወሓት ጋር የገጠመው የኢትዮጵያ ሠራዊት፤ ከጠላት የሰው ኃይል ቁጥር እና ትጥቅ ያነሰ ነገር ግን ኢትዮጵያዊነትን ስንቁ ያደረገ እንደነበርም ተናግረዋል።

ከአሸባሪው ህወሓት ጋር እየተደረገ ያለው ጦርነት አልተጠናቀቀም ያሉት ጀነራል አበባው ሠራዊቱ የምዕራፍ አንዱን ጦርነት አጠናቅቆ ለቀጣይ ግዳጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን አሁንም ትንኮሳውን እንዳላቋረጠም ነው ጀነራሉ የተናገሩት።

አሸባሪው ህወሓት ተቆጣጥሯቸው ከነበሩ አካባቢዎች በማስወጣት የተገኘው ድል ህዝባዊ ድል ነው ያሉት ጀነራሉ የጠላትን የማድረግ አቅም ያዳከመ እና ከፍተኛ የሰው ኃይል እና የንብረት ኪሳራ ያደረሰ መሆኑንም ገልፀዋል።

በጋሸና፣ ሚሌ እና በመሀል ግንባሮች ፈታኝ ውጊያዎች ተደርጎ እንደነበር የገለፁት ጀነራሉ ሠራዊቱ ከፍተኛ ጀብዱ የሰራባቸው እንደነበሩም ተናግረዋል።

ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሩ የወሰደው ቁርጠኝነት የሠራዊቱን ዝግጁነት አቅም ያሳደገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም