በሐዋሳ ከበዓሉ ታዳሚዎች ስልክ ነጥቆ ለመሰወር የሞከሩ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

102

ሐዋሳ፣  ጥር 11 /2014 (ኢዜአ) በሐዋሳ ከተማ ከበዓሉ ጥምቀት በዓል ታዳሚዎች ስልክ ነጥቆ ለመሰወር የሞከሩ ሁለት ግለሰቦች እጅ ከፍንጅ ተይዘው በሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስር መቀጣታቸውን ፖሊስ ገለጸ ።

የሲዳማ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተስፋዬ ቱንጋሞ ሐዋሳን ጨምሮ በሁሉም የገጠርና ከተማ መዋቅሮች በዓሉ በሰላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ የፀጥታ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በተለይም ሐዋሳ ከተማ በርካታ የሀገር ውስጥና ከውጭ የመጡ የእምነቱ ተከታዮች የሚታደሙበት በዓል በመሆኑ ያለምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከበር የተቀናጀ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በዚህም በዓሉ በሰላም እንዲከበር በየቀበሌ ወጣቶች በግንባር ቀደምነት የተሳተፉበት የፀጥታ አደረጃጀት መዘርጋቱን አብራርተዋል።

የሚፈጸሙ ወንጀሎች ካሉ አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት የሚያስችል በፖሊስና ዐቃቤ ህግ ጥምረት አስቸኳይ ችሎት ተቋቁሞ ስራዎችን ሲያከናውን መዋሉንም ገልጸዋል።

በእስራት የተቀጡት ግለሰቦች በሐዋሳ ከተማ ከባህረ ጥምቀቱ ከሚመለሱ ሁለት ሰዎች የሞባይል ስልክ ቅሚያ ወንጀል መፈጸሙን ተናግረዋል።

ፖሊስ ከኅብረተሰቡ ጋር በመተባበር ባደረገው ክትትል ግለሰቦቹን እጅ ከፍንጅ ተይዘውና በችሎቱ ተመስክሮባቸው ጥፋተኛ በመሆናቸው የሁለት ዓመት ከስድስት ወር እስራት መቀጣታቸውን ገልጸዋል።

የጥምቀት በዓል በሲዳማ ክልል በሁሉም አካባቢዎች ካለምንም የፀጥታ ችግር በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን ኮሚሽነር ተስፋዬ አረጋግጠዋል።

በህዝብ አደረጃጀት እየተረጋገጠ ያለው ጠንካራ ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ፖሊስ ከህዝብ ጋር በመሆን ወንጀል የመከላከሉን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፀጥታ ኃይሎች፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና በአስቸኳይ ችሎት ስራ ለተሰማሩት ሁሉ ኮሚሽነር ተስፋዬ አመስግነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም