በጥምቀት ስነ-ስርአት ላይ ስርቆት በመፈጸምና የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት የተከሰሱ ተቀጡ

78

ጎንደር ፣ጥር 11/2014 (ኢዜአ)- በጎንደር ከተማ በጥምቀት በዓል አከባበር ስነ-ስርአት ላይ የስርቆት ወንጀል በመፈጸምና የጦር መሳሪያ ይዞ በመገኘት የተከሰሱ ግለሰቦች በእስራትና በገንዘብ መቀጣታቸውን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በጎንደር በታላቅ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ስርአት የተከበረው የጥምቀት በአል በሰላም ተጠናቋል፡፡

የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ ሊቀጡ የቻሉት የፈፀሙት ወንጀል በማስረጃ በመረጋገጡ ነው።

በበአሉ አከባበር ስነ ስርአት ላይ ዘረፋ የፈፀመ አንድ ግለሰብንና በተከለከለ ስፍራ የጦር መሳሪያ ይዞ የተገኘ ሌላ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውለው በጥምቀተ ባህሩ ለተቋቋመው ጊዚያዊ ችሎት መቅረባቸውን ተናግረዋል።

ችሎቱ ባካሄደው ፈጣን የወንጀል ክስ ማጣራት ሂደት በበአሉ ስነ ስርአት ላይ ከአንድ ግለሰብ ኪስ የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ሲሰርቅ እጅ ከፍንጅ በተያዘ ግለሰብ ላይ የአንድ አመት ከስድስት ወር እስራት የቅጣት ውሳኔ ማስተላላለፉን ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ አስታውቀዋል፡፡

ችሎቱ በተጨማሪም በአዘዞ ክፍለ ከተማ የተከለከለ የጦር መሳሪያ በመያዝ ታቦት ሲያጅብ የተገኘ ሌላ ግለሰብ በአንድ ሺህ ብርና በስምንት ወር የእስራት ገደብ እንዲቀጣ መወሰኑን ዋና ኢንስፔክተሩዋ ተናግረዋል፡፡

በጎንደር ከተማ እንግዶችና የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት በታላቅ ስነ ስርዓት ለሚከበረው የጥምቀት በዓልም ሰላማዊነት ቀደም ብሎ የተቀናጀ መደረጉን ጠቁመው በአሉ በሰላም መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

የከተማው ህዝብ በተለይም ወጣቱ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት የከተራና የጥምቀት በአል በሰላም እንዲጠናቀቅ ከፖሊስና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በመቀናጀት ከፍተኛ ትብብር ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

በዓሉ በሰላማዊ መንገድ ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል ።

በነገው እለት በሚካሄደው የሚካኤል ታቦት የማስገባት ስነ-ስርአት ህዝቡ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስ መልእክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም