የኢትዮጵያን አስደናቂ ቅርሶች ለመጠበቅ ዩኔስኮ የተጠናከረ ድጋፍ ያደርጋል

221

ጥር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያን አስደናቂ ቅርሶች ለመጠበቅ የተጠናከረ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) ዳይሬክተሯ ዩኒኮ ዩኮዚኪ ተናገሩ።

በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ በተከናወነው የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ የተገኙት ዳይሬክተሯ፤ ኢትዮጵያ የበርካታ አስደናቂ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት መሆኗን ተገንዝቢያለሁ ብለዋል።

የኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅርና የአብሮነት መገለጫዎች ሆነው የቀጠሉ ቅርሶች መኖራቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያ መንግስት ለቅርሶቹ የሚያደርገውን ጥበቃ አደንቃለሁ ብለዋል።

ቅርሶቹ ተጠብቀው ከትውልድ ትውልድ እንዲተላለፉ በማድረግ የኢትዮጵያዊያን ሃላፊነት የላቀ መሆኑን ገልጸው የኢትዮጵያን አስደናቂ ቅርሶች ለመጠበቅ ዩኔስኮ የተጠናከረ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው በበኩላቸው የጥምቀት በዓልን ይዘቱንና ክብሩን በማስጠበቅ ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።

በዓሉ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ ዛሬ ላይ የደረሰ ዓመታዊ ሁነት መሆኑን ገልጸው በዓሉ ስርዓቱን ጠብቆ እዚህ እንዲደርስ አበርክቶ ያደረጉ ወገኖች ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

የቀደምት አያቶች በዓሉ የሚያዘውን ፍቅርና ትህትና፣ ህብረትና መተሳሰብን፣ መረዳዳትና መደጋገፍን፣ ቱባ ባህልና ጥበብን እንዲሁም ሌሎች በርካታ የመልካም ስነ-ምግባር መገለጫዎችን አስረክበው ማለፋቸውን ተናግረዋል።

በዓሉን የተረከበው የአሁኑ ትውልድም እንደ ቀደምት አያቶች ሁሉ በመንከባከብና እሴቱን በመጠበቅ ለቀጣይ ትውልድ ማሸጋገር አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በመንግስትም በኩል ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ጠቅሰው እስካሁን ሲያደርግ የነበረው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ችግሮች ካሉ ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼