በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ምእራባዊያን ሚዲያዎች እንደሚሉት ሳይሆን ሰላምና መረጋጋት የሚታይበት፣ በዓላት በድምቀት የሚከበሩበት ነው

197

ጥር 11 ቀን 2014 (ኢዜአ) “በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ አንዳንድ ምእራባዊያን ሚዲያዎች እንደሚሉት ሳይሆን ሰላምና መረጋጋት የሚታይበት፣ በዓላት በድምቀት የሚከበሩበት ነው” ሲሉ ከአሜሪካ በመምጣት በጥምቀት በዓል ላይ የተገኙት ፓስተር ሮቨን ኤሊ ውድስ ተናገሩ።

ፓስተር ሮቨን ኤሊ ውድስ፤ በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የጥምቀት በዓል ላይ ለመገኘት ከ20 በላይ የልዑካን ቡድን አባላትን ይዘው በኢትዮጵያ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያን አውነታ በማዛባት የሃሰት መረጃ ያሰራጩ የነበሩትን አካላት ጉት ጎታ ችላ ብለው አገር ቤት የገቡ በርካታ ዳያስፖራዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች በተገኙበት የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

ከአሜሪካ ቨርጅኒያ ግዛት በሚገኝ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁኔር ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን ከ20 በላይ ልዑክ አባላትን ይዘው የመጡት የሃይማኖት መምህሩ ፓስተር ሮቨን ኤሊ ውድ፤ በጃን ሜዳ በተካሄደው የጥምቀት በዓል አከባበር ላይ ተገኝተዋል።

በባህላዊ ገጽታዎች እና በርካታ ምእመናን ታጅቦ በድንቅና ማራኪ ክንውን በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ ተገኝተው በዓሉን በማክበራቸው በእጅጉ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

አብረዋቸው ካሉት ልኡካንም ብዙዎቹ ወደ አፍሪካ ሲመጡ የመጀመሪያቸው መሆኑን ጠቅሰው በክብረ በዓሉ ላይ በተመለከቱት ሁሉ ትልቅ መንፈሳዊ ሃሴት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

ለኢትዮጵያ አጋርነታቸውን ለማሳየት ስለመምጣታቸው የተናገሩት ፓስተር ሮቨን፤ በቀጣይም ልኩካንን በመያዝ የኢትዮጵያን ድንቅ ኃይማኖታዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶች የማስተዋወቅ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊያን ፈጣሪያቸውን የሚፈሩ፣ በጀግንነታቸው የሚጠቀሱ፣ አገራቸውን በቅኝ ገዥዎች ያላስደፈሩ መሆኑን አስታውሰው ለማንም የውጭ ሃይል የሚንበረከኩ አይደሉም ሲሉ ተናግረዋል።

እኛም ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ እነዚህንና ሌሎች አስደናቂ ታሪኮቿን በቅጡ ተገንዝበን ነው ብለዋል።

በአንዳንድ ምዕራባዊያን ሚዲያዎች ስለ ኢትዮጵያ ይሰራጭ የነበረውን የማስፈራሪያ መልእክት ስንሰማ ቆይተን በአካል ስንገኝ ግን ፍፁም የተለየ ሆኖ አግኝተነዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ሰላምና መረጋጋት የሚታይበት፣ በዓላት በድምቀት የሚከበሩበት፣ ኢትዮጵያዊያን እንግዶቻቸውን በፍቅር ተቀብለው የሚያስተናግዱበት ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያን በሚመለከት ከእውነታው በመራቅ ዓለምን የምታደናግሩ ሚዲያዎች ከስህተታችሁ ልትታረሙ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼