የጥምቀት በዓል 44 ታቦታት በአንድ ላይ ሆነው በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል

121

 አዲስ አበባ፣ ጥር 11/2014 (ኢዜአ )  የጥምቀት በዓል 44 ታቦታት በአንድ ላይ ሆነው በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

በክብረ በዓሉ ላይ ብጹዐን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ዘማሪያን እና በርካታ ምዕመናን በተገኙበት ተከብሯል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በመገኘት መልእክት ያስተላለፉት የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረጻዲቅ፤ የጥምቀት በዓል ከሃይማኖታዊ እሴቱ በተጨማሪ አይነተኛ የቱሪስት መስህብ ሆኗል ብለዋል።

በምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ የሚከበረው የጥምቀት በዓልም ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ታሪካዊ መሆኑን ጠቅሰው የበርካቶችን ቀልብ እየገዛ መሆኑን ገልጸዋል።

በስፍራው የበዓሉን አከባበር ሰፊ የቱሪስቶች መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸው የአካባቢው ማህበረሰብም ለቱሪስቶች ምቹና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የበርካቶች መዳረሻ እንዲሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የጥምቀት በዓልም ከጥንት ጀምሮ በኢራንቡቲ እየተከበረ መዝለቁን ጠቅሰው እንደ ቆይታው ብዙም ትኩረት ሳያገኝ ቆይቶ አሁን ላይ ግን በስፋት እየታወቀ መጥቷል ብለዋል።

የምንጃር ሸንኮራ አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ቦሴት በበኩላቸው በኢራንቡቲ የሚከበረውን የጥምቀት በዓል ከእምነቱ ስርዓት ባሻገር ወረዳውን ከማስተዋወቅ አንጻር ከፍተኛ ድርሻ እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።

ለቀጣይም የበለጠ እንዲተዋወቅ እና በርካታ ጎብኚዎች የሚገኙበት እንዲሆን የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

የጥምቀት በዓል በኢራንቡቲ 44 ታቦታት በተገኙበት የተከበረው ዘንድሮ ለ620ኛ ዓመት መሆኑ ታውቋል።

በኢትዮጵያ የጥምቀት በዓል አከባበር በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በዩ.ኔ.ስ.ኮ. የተመዘገበ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም