በጎንደር ከተማ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች እንደሚሰሩ ተገለጸ

91

ጎንደር፣ ጥር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) ''በጎንደር ከተማ የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው ይሰራሉ'' ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከጎንደር ከተማ የህዝብ ተወካዮች ጋር በሰላምና ልማት ላይ አተኩረው ማምሻውን በተወያዩበት ወቅት እንዳሉት፤ ህዝቡ አደረጃጀቶችን መሰረት አድርጎ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ሊያጠናክር ይገባል።

አስተማማኝ ሰላም ለልማት መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ "የክልሉ መንግስት ለጎንደር ከተማ ልማት መፋጠን ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል" ብለዋል።

በተለይ የከተማውን የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የአንገረብ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

ሌሎች የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎችም ደረጃ በደረጃ እንደሚከናወኑ ነው ዶክተር ይልቃል አስታውቀዋል።

የከተማው የህዝብ ተወካይና የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ተቀባ መንግስቴ በበኩላቸው በከተማው የሚስተዋሉ የኤሌክትሪክ፣ የውሃና ሌሎች መሰረተ ልማት ችግሮች ቅድሚያ ተሰጥቶ እንዲፈቱ ጥያቄ አቅርበዋል።

የወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር በዘላቂነት እንዲፈታና የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችም ትኩረት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም