በዞኑና በከተማው የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል-ፖሊስ

150

ነቀምቴ/ጭሮ ጥር 10/2014 /ኢዜአ/የጥምቀት በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ዝግጅት ማድረጋቸውን የምሥራቅ ወለጋ ፖሊስ መምሪያና የጭሮ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት አስታወቁ ፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን ፖሊስ መምሪያ የአካባቢ ጸጥታ ማረጋገጥ ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ደረጀ ወንድሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ዝግጅት ተደርጓል።

በሁሉም ወረዳዎች በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ የእምነቱ ተከታዮች ያለምንም የፀጥታ ሥጋት በድምቀት እንዲያከብሩ ከሕብረተሰቡ ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

እንደ ኮማንደር ደረጀ  ጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ በተቀናጀ አግባብ የጸጥታ ማስከበር ተግባር መፈጸም የሚችሉበት ስምሪት ተደርጓል።

ሠላም የሚረጋገጠው በፀጥታ አካላት ብቻ ባለመሆኑ የዞኑ ሕዝብ ከፀጥታ አካላት ጎን በመቆም የራሱንና የአካባቢውን ሠላምና ጸጥታ እንዲያስከብር ጠይቀዋል።

ምእመናን በአሉ በሚከበርበት ስፍራ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በማድረግ እራሳቸውንና ሌሎችን ከኮሮና እንዲጠብቁ  ኮማንደር ደረጀ አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ የጥምቀት በዓል ያለ ምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የጭሮ ከተማ ፖሊስ አስታውቋል፡፡

የከተማው ፖሊስ አዛዥ ዋና ሳጂን ካሳሁን ባይሳ እንደገለጹት በዓሉ በሰላም በሚከበርበት ሁኔታ ላይ ከፀጥታ አካላትና ከሀይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ተደርጎ ወደ ስራ ተገብቷል።

የጭሮ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሾይቢ ሐምዛ በበኩላቸው የከተማው ወጣቶች የፀጥታ ማስከበር ሥራው አካል መደረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም