የከተራ በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከበረ ነው

145

ጥር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) የከተራ በዓል በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደመቀ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡

ድሬዳዋ፣ ሀዋሳ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ደብረ ብርሃን፣ ሰቆጣ፣ ሐረር፣ ጭሮ፣  ነቀምቴ፣ ጅማ እና  በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች  ታቦታት ከየደብሩ ወደ ጥምቀተ ባህር በማቅነት የከተራ በዓሉ  ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ጠብቆ  እየተከበረ መሆኑን የኢዜአ ሪፖርተሮች ከየሥፍራው ዘግበዋል።

በድሬዳዋ በብዙ ሺ የሚገመቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተከታዮችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች  ከአራቱ ማዕዘናት ከሚገኙ አድባራት ወደ ባህረ-ጥምቀቱ የተጓዙ ታቦታትን አጅበው የከተራ በዓል እያከበሩ ናቸው፡፡

በበዓሉ ላይ የተሣተፉ የእምነቱ ተከታዮች የከተራና የጥምቀት በዓልን በመረዳዳትና የተቸገሩትን በማብላትና በማልበስ ያላቸውን አጋርተው እንደሚያሳልፉ ለኢዜአ  ተናግረዋል፡፡

በዓሉ በሰላምና በፍቅር እንዲከበር ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ በሀዋሳ ከተማ የከተራ በዓል በደማቅ  ሥነ-ሥርዓት  እየተከበረ ነው።

ታቦታቱ ከየአአጥቢያቸው በመነሳት በካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምዕመናን ታጅበው ወደሚያድሩበት ደብረ ምጥማክ መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን  አቅንተዋል።

የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃውንት በዓሉን የተመለከተ ያሬዳዊ ጥዑመ ዜማ እንዲሁም የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን የምስጋና ህብረ ዝማሬ እያቀረቡ ታቦታቱን አጅበው ወደ ማደሪያው አድርሰዋል።

በሐረሪ ክልል የከተራ በዓል በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ሲሆን ታቦታት በሚወጡባቸው ሁሉም አቅጣጫዎች ምዕመኑ በመዝሙርና ፈጣሪያቸውን በማወደስ  ጥምቀተ ባህሩ ደርሰዋል። 

በክብረ በዓሉም ምዕመናኑ ሃይማኖታዊ ስነ ስርዓቱን ባከበረ መልኩ እና የጋራ የጸጥታ ስራ በማከናወን የከተራ በዓሉን እያከበሩ ነው። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም