44ቱ ታቦታት በጋራ በሚያድሩበት ምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ ባህረ ጥምቀት የከተራ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው

329

ጥር 10/2014/ኢዜአ/ 44ቱ ታቦታት በጋራ በሚያድሩበት ምንጃር ሸንኮራ ኢራንቡቲ ባህረ ጥምቀት የከተራ በዓል በድምቀት እየተከበረ ነው፡፡

የጥምቀት በዓላት በድምቀት ከሚከበሩባቸው አካባቢዎች መካከል በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ኢራንቡቲ አንዱ ሲሆን፤ 44 ታቦታት በጥምቀት ማክበሪያ ስፍራ ላይ የሚገናኙ ይሆናል።

ታቦታቱ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በካሕናቱ አኮቴት፣ ምስጋና እና በሊቃውንት ሽብሻቦ፣ በምዕመናንና በዘማሪያን እልልታ፣ ታጅበው ወደ ማደሪያቸው እያመሩ ይገኛሉ።

በኢራንቡቲ የጥምቀት በዓል ሲከበር ለ620ኛ ጊዜ መሆኑን የምንጃር ሸንኮራ ባህልና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ዋልታንጉስ ዘርጋው ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህ ስፍራ የሚገኘው የጥምቀት በዓል ማክበሪያ ወንዝም ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት ባህረ ዮርዳኖስ የተሰየመ ሲሆን "ዳግማዊ ዮርዳኖስ" እየተባለ ይጠራል፡፡

በኢራንቡቲ የጥምቀት በዓልን ለማክበር ከመንበረ ክብራቸው ከሚወጡት ታቦታት መካከል የሸንኮራ ዮሐንስ፣ ባልጪ አማኑኤል እና በሳ ሚካኤል ይገኙበታል።

በኢራንቡቲ የሚከበረው የጥምቀት በዓል በአጼ ልብነ ድንግል ዘመነ መንግስት በኢትዮጵያ ከሚከበሩ ደማቅ የጥምቀት በዓላት መካከል አንዱ እንደሆነ ተነግሯል።

ኢራንቡቲ ከአዲስ አበባ በሞጆ በኩል በ147 ኪሎሜትር ላይ የምትገኝ ሲሆን በደብረብርሃን በኩል ደግሞ በ276 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም