ወደ አገር ቤት የመጡ የዳያስፖራ አባላት ለመከላከያ ሰራዊት 50 ሰንጋዎችን ድጋፍ አደረጉ

73

ጥር 10/2014/ኢዜአ/ ወደ አገር ቤት የመጡ የዳያስፖራ አባላት ለመከላከያ ሰራዊት የሶስት ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸውን 50 ሰንጋዎች ድጋፍ አደረጉ፡፡

ዳያስፖራዎቹ ድጋፉን ያደረጉት በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ያሉ ወዳጆቻቸውን አስተባብረው መሆኑም ተገልጿል፡፡

ዳያስፖራዎቹ ባሉበት አገር ሆነው 'ኢትዮጵያ ትቀጥላለች' በሚል ሀሳብ የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርጉ መቆየታቸውም ነው የተገለጸው፡፡

ከዳያስፖራዎቹ ተወካዮች አንዱ በአሜሪካን አገር ነዋሪ የሆኑት ዶክተር ማርቆስ አደሞ ካሉበት አገር ሆነው የለውጡን መንግስት ሲደግፉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

አሁንም ከዳያስፖራና አገር ውስጥ ካሉ ወዳጆች ባሰባሰቡት ሶስት ሚሊዬን ብር ሰንጋ በሬዎችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም በሚችሉት አቅም ሁሉ ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጎን ሆነው ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን እያከናወኑ መሆኑን የሚናሩት አቶ ደፎ መብራት የአገር ፍቅርን በተግባር ማሳዬት ተገቢ መሆኑን ይጠቅሳሉ።

ሁል ጊዜ ቅሬታ ከማቅረብ ይልቅ በሚቻለው አቅም ለአገር ልማት፣ እድገትና ቀጣይነት መረባረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዛሬም በዓሉን ምክንያት በማድረግና የመከላከያ ሰራዊት ለማገዝ በማሰብ ይህን ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ድኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፤ዳያስፖራው ኢትዮጵያን በሚያስተሳስሩ፣ አንድ በሚያደርጉና በሚያበለጽጉ ተግባር ላይ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በቀጣይም መንግስት የመከላከያ ሰራዊትን ለማጠናከር በሚያከናውናቸው ተግባራት ላይ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡

በርካታ የዲያስፖራ ማሕበረሰብ አባላት በተደረገው ጥሪ መሰረት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም