በኢትዮጵያ በዲጅታል ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ሰፊና አዋጭ እድል አለ

438

አዲስ አበባ፣ ጥር 10 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በዲጅታል ቴክኖሎጂ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል ሰፊና አዋጭ እድል መኖሩን በኢትዮጵያ በዘርፉ ኢንቨስት ያደረጉ የዳያስፖራ አባላት ተናገሩ፡፡

ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ ሙያተኛ ዳያስፖራዎች ትናንት ማምሻውን የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ መስሪያ ቤትን የጎበኙ ሲሆን፤  ከኤጀንሲው አመራሮች ጋር በጋራ ለመስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይም ተወያይተዋል።

ከጉብኝቱ በኋላ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የተናገሩ የዘርፉ ሙያተኞች የዲጅታል ዘርፍ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በርካታ ወጣቶችን እና ሰፊ የገበያ አማራጭ በያዙ አገራት እጅግ አዋጭ ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የሳይበሩ ዓለም የአገር ሁለንተናዊ አቅም መገንቢያ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ አኳያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን በመታጠቅ የሳይበር ሉዓላዊነትን ማስከበርና ደህንነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

ከ30 ዓመታት በላይ በጀርመን አገር የኖሩት ዶክተር ብርሐኑ በየነ፤ ዳያስፖራው የኢትዮጵያን አሁናዊ ሁኔታ ተረድቶ በየተሰማራበት የሙያ መስክ የራሱን አሻራ ለማሳረፍ ጥሪውን ተቀብሎ መምጣቱን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ደግሞ ከፍተኛ የሳይበር ጥቃት ዒላማ መሆኗን ጠቅሰው፤ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት ለማስጠበቅና ሁለንተናዊ አቅሟን ለመገንባት ደግሞ ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን አብሮነት ይጠይቃል ነው ያሉት።

በዚሀም በቅርቡ እርሳቸው የሚመሩት የኢትዮጵያ ሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች ማህበር መቋቋሙን ገልጸው፤ ማህበሩ በዘርፉ ሰፊ ልምድና ዕውቅት ያላቸውን ዳያስፖራዎች በአባልነት እያሰባሰበ መሆኑን ተናግረዋል።

የሳይበሩ ዘርፍ በመከላከያም፣ በዜጎች ደህንነት፣ በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው፤ በዘርፉ ላይ መሰማራት ደግሞ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ለመሰማራት ከፍተኛ መነሳሳት እያሳየ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

በአሜሪካ ፔንስሌቪኒያ የሚገኘው “ኤክሰለረንስ ቴክኖሎጂ ሶሊዩሽን” በተሰኘው ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ መላኩ በሻህ ዲጂታል ቴክኖሎጂ አገርን በአጭር ጊዜ ከሚያሳድጉና አገራዊ አቅም ከሚገነቡ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከሶስት ዓመታት በፊት ደርጅቱ በቴክኖሎጂ ዘርፍ በኢትዮጵያ ኢንቨስት ማድረጉን ገልጸው፤ በየዓመቱ በዘርፉ ሰልጥኖ የሚመረቅ ሰፊ የሰው ኃይል ባላት ኢትዮጵያ የጂጂታል ዘርፍ መሰማራት አዋጭ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በዘርፍ ላይ ይበልጥ በመስራት አገር እና ወገን ለመደገፍ ትክክለኛው ጊዜ አሁን መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

አቶ አማኑኤል አባይነህ በበኩላቸው ቀደም ብሎም ወደ አገር ቤት በመግባት በዘርፉ ላይ እየሰሩ ስለመሆኑ ገልጸው፤ የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ በዘርፉ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አድንቀዋል፡፡

የሳይበር ዘርፍ የወቅቱ ትኩረት በመሆኑ ከወዲሁ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባም ነው ያነሱት፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ የልጆቿን እውቀት፣ የቴክኖሎጂ ክህሎትና ዕምቅ አቅም የምትሻበት ትክክለኛ ጊዜ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የዲጅታል ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው የቴክኖሎጂ ባለቤት በመሆን ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ከዚህ አኳያ ዳያስፖራው በግልም ሆነ በድርጅት የኢትዮጵያን ሳይበር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከኤጀንሲው ጋር በጋራ እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።

የሳይበር ምህዳር ሰፊና ተለዋዋጭ በመሆኑ የዘርፉ ባለሙያዎች ዳያስፖራዎች ያላቸውን ልምድና የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲያጋሩና በዘርፉ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሰማሩም እንዲሁ፡፡