ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው

59

ሚዛን፣ ጥር 9/2014 (ኢዜአ) ሀገሪቱ ያጋጠማትን ፈተና በመቋቋም ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ጋር በህብረተሰብ ጤና አጠባበቅ ዙሪያ ዛሬ በቦንጋ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ  "እንደ ሀገር የገጠመንን ፈተና በጽናት በመቋቋም የህብረተሰባችንን ጤና ለማስጠበቅ እየሰራን ነው" ሲሉ በውይይቱ ላይ አስታውቀዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል  አዲስ እንደመሆኑ መጠን ከሚመለከታቸው አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በክልሉ የሚታዩ የጤና ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ  ተናግረዋል።

በተለይ  ለህብረተሰቡ የጤና አገልግሎትን በጥራት ተደራሽ ለማድረግ እንዲቻል ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የዓለም ጤና ድርጅት ተወካዮች፣ በጤና ላይ የሚሰሩ አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ሚኒስትር ደኤታው ከውይይት መድረኩ በተጓዳኝ በቦንጋ ከተማ የሚገኘውን የገብረ ጻዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ጎብኝተዋል።

 በጉብኝቱ ወቅት ሆስፒታሉን ወደ ሪፈራል ለማሳደግ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

ሆስፒታሉ እንደ ሀገር ተወዳዳሪ የህክምና ተቋም መሆኑን ዶክተር ደረጀ ጠቅሰው የአገልግሎት አሰጣጡን  ይበልጥ ለማሻሻል ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በበኩላቸው በክልሉ በሚገኙ ሆስፒታሎችና ሌሎችም የጤና ተቋማት ውሰጥ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ጎልቶ እንደሚታይ ጠቁመዋል።

የጤና ሚኒስቴርና አጋር ድርጅቶች ችግሩን ከግንዛቤ በማስገባት የመድኃኒት አጥረቱ እንዲፈታ ለክልሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም