ሚኒስቴሩ በኢትዮጵያ ያሉ የኢነርጂ አቅሞችን የሚያመላክት መተግበሪያ ይፋ አደረገ

96

አዲስ አበባ፣ ጥር 9/2014( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በተለያዩ መልክዓ-ምድሮች ያሉ የኢነርጂ አቅሞችን የሚያመላክት "ኢነርጂ አክሰስ ኤክስፕሎረር" የተሰኘ መተግበሪያ ይፋ አደረገ፡፡

መተግበሪያው የበለጸገው "ወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩሺን እና አፍሪካ ኪሊን ኢነርጂ" በተሰኙ ኩባንያዎች   ሲሆን፤ ሚኒስቴሩ በዛሬው እለት መተግበሪያውን በይፋ ስራ አስጀምሯል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሐብታሙ ኢተፋ በዚህን ወቅት መተግበሪያው በዋናነት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የኢነርጂ አቅሞችን የተመለከተ መረጃ የሚሰጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚካሄዱ ልማቶች የሚውሉ የኃይል አማራጮችን በማመላከት ልማትን ለማፋጠን እንደሚያግዝም እንዲሁም፡፡

በተጨማሪ የኃይል እጥረት ባለበት አካባቢ ከግሪድ ኃይል አቅርቦት ወጭ ያሉ አማራጮችን በመጠቆም ኃይል ተደራሽ  ለማድረግ እንደሚያግዝም ተናግረዋል፡፡፡

ሚኒስትሩ አያይዘውም የግሉ ዘርፍ ከመንግስት ጋር በመቀናጀት በኃይል ልማት ላይ እንዲሳተፍ የሚፈቅድ አዋጅ መጸደቁን ጠቁመው፤ይህም በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ ዘርፉ በመቀላቀል የኃይል እጥረትን በመቅረፉ ረገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ያግዛል ነው ያሉት፡፡

እስካሁን ባለው ሂደት ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ህዝብ ውስጥ የኃይል ተጠቃሚ የሆነው 55 በመቶ ብቻ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2025 ከንፋስ፣ ከፀሀይ፣ ከጂኦ-ተርማልና ከውሃ የኃይል አማራጮችን በመጠቀም  ለዜጎቿ ሙሉ በሙሉ ኃይል ተደራሽ የማድረግ ግብን አስቀምጣ እየሰራች መሆኑን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም