"አባቴ አደራ የሰጠኝ ቤተሰቦቼን ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሰንደቅ ዓላማዋን ነው"

141

ጥር 8/2014/ኢዜአ "አባቴ አደራ የሰጠኝ ቤተሰቦቼን ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሰንደቅ ዓላማዋን ነው" በማለት የጀግናው ሻለቃ አብይ ጋሹ ልጅ ምክትል መቶ አለቃ ሕይወት አብይ ትናገራለች።

"አባቴ ከሁሉ አብልጦ አደራ የሰጠኝ ቤተሰቦቼን ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሰንደቅ ዓላማዋን ነው" ትላለች ለአገሩ በክብር የተሰዋው፤ በዚህም አንደኛ ደረጃ "የላቀ ጀግና" የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚው የጀግናው ሻለቃ አብይ ጋሹ ልጅ ምክትል መቶ አለቃ ሕይወት አብይ።

ላብ ከደም ገብሮ ሀገርን በክብር ለማቆም ከቆረጠ ሰው በላይ ጀግና ከወዴት ይገኛል?

ለሀገር ወጥቶ ከማደር፣ ለሉአላዊነቷ እንቅልፍ ከማጣት፣ ለነጻነቷ ከመሰዋት በላይስ የሀገር ፍቅር በምን ይገለጻል?

የኢትዮጵያ የሉአላዊነቷ የመጨረሻ ምሽግ የሆነው የጀግናው መከላከያ ሰራዊት አባላት ዘንድ የኢትዮጵያዊነት ጥጉ ይህ ነው።  

እንደ ሻለቃ አብይ ጋሹ የበኩር ልጅን ተተኪ አድርጎ ለሀገር ዘብነት እስከማጨት በሚደርስ ፍቅር የሚገለጽ ኢትዮጵያዊነት።

ሻለቃ አብይ ጋሹ ሕይወቱን ገብሮ ኢትዮጵያ በክብሯና በማዕረጓ ሕዝቦቿ በአንድነትና በሠላም እንዲኖሩ ታግሎ በግንባር የተሰዋ ጀግና ነው።

በተሰለፈባቸው አውደ ውጊያዎች ሁሉ ክንደ ብርቱነቱን ያስመሰከረ በጀግንነት ሰገነት ላይ የወጣ እናም ለአገሩ ክብር ሕይወቱን የከፈለ የሀገር ባለውለታ ነው።

የ41 ዓመቱ ጎልማሳ ሻለቃ አብይ አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን አፈርሳለሁ ብሎ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች እየተፋለመና እየደመሰሰ በኢትዮጵያ ህልውና ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ በመቀልበስ የበኩሉን ደማቅ ታሪክ ጽፎ በጋሸና ግንባር የሕይወት ዋጋ የከፈለ እንቁ የኢትዮጵያ ልጅ ነው።

መንግስት ለአገር ህልውና አለኝታና መከታ በመሆን የሕይወት መስዋዕትነት ለሚከፍለው የአገር መከላከያ ሠራዊት  እውቅና ሲሰጥ የህይወት መስዋእትነት እስከመክፈል የደረሰ አኩሪ ገድል የፈጸመው ሻለቃ አብይ የአንደኛ ደረጃ የላቀ ጀግና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበር።

እውቅናውን ልጁ ምክትል መቶ አለቃ ሕይወት አብይ ከፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እጅ ተቀብላለች።

ኢዜአ ከምክትል መቶ አለቃ ሕይወት አብይ ጋር በአባቷ የጀግንነት ገድል እና እውቅናው በቤተሰባቸው ዘንድ የፈጠረው ስሜት ምን እንደሚመስል በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝቶ ቆይታ አድርጓል።

የሶስት ልጆች አባት የሆነው ሻለቃ አብይ ለአገሩ ካለው ፍቅር የተነሳ የበኩር ልጁ ተተኪው እንድትሆን ከእርሷ ጋር ተማክሮ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን አቋርጣ መከላከያ ሠራዊትን እንድትቀላቀል አድርጓል።

ምክትል መቶ አለቃ ሕይወት አብይ ጋሹ አባቴ ከመሞቱ በፊት ደውሎ አደራ የሰጠኝ ቤተሰቦቼን ሳይሆን ኢትዮጵያንና ሰንደቅ ዓላማዋን ነው ትላለች።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የሀይድሮሊክስ ኢንጅነሪንግ ትምህርት እየተከታተለች በነበረበት በ2012 ዓ.ም በወጣው አገራዊ ጥሪ መሰረት ከአባቷ ጋር ተማክራ መከላከያን በዕጩ መኮንንነት መቀላቀሏን ትናገራለች።

ሻለቃ አብይ በግንባር ሆኖ ለበኩር ልጁ ምክትል መቶ አለቃ ሕይወት ስልክ በመደወል "ቤተሰቦቼ ሳትይ ኢትዮጵያንና ባንዲራዋን ጠብቂ" ሲል አደራ እንደሰጣት ትናገራለች።

የሻለቃ አብይ የአገር ፍቅር ስሜት ዛሬ በበኩር ልጁ ሲገለጥ 'አባቴ ስለ አገር ክብር በጀግንነት የተሰዋ በመሆኑ በመሰዋቱ ሀዘን ቢሰማኝም ለኢትዮጵያ ክብር በጀግንነት የተሰዋ በመሆኑ እኮራለሁ" ነው ያለችው።

ለኢትዮጵያ መሰዋት ክብር መሆኑን የገለፀችው ምክትል መቶ አለቃ ሕይወት "እኔም የአባቴን ፈለግ መከተል እፈልጋለሁ" ትላለች።

የ4ኛ ክፍል ተማሪዋ ህፃን ሀዊ አብይም "አባቴ ለኢትዮጵያ ሲል ነው የተሰዋው አባቴ አልሞተም ጀግና ነው" በማለት ነው የገለጸችው።

ልጆቹ የአባታችንን ፈለግ ተከትለን ለአገራችን ዘብ እንቆማለን ስትል በህፃን አንደበቷ ትናገራለች።

"አባቴ ያው ወታደር ነው ለኢትዮጵያ ሲል ነው የተሰዋው። አባቴ ጀግና ነው አልሞተም፤ የእሱን ፈለግ ተከትለን እኔም እሷም ወንድሜም አሁንም ነገም ዛሬም እንከተላለን።"

በ24 ዓመታት የትዳር ቆይታ 3 ልጆችን ማፍራት የቻሉት የሻለቃ አብይ ባለቤት ወይዘሮ ዘላለም ምንተስኖት፤ ባለቤቴ አገር ወዳድ፣ በአገሩ ድርድር የማያውቅ ጀግና ነው ይላሉ።

በእርግጥ የልጆቼን አባት ግማሽ አካሌን ያጣሁ ቢሆንም በአገሩ የማይደራደር ቅድሚያ ለአገሩ የሚሰጥ በመሆኑ በፈፀመው ጀብዱ ኮርቻለሁ በዚህም እጽናናለሁ ብለዋል።

የሻለቃ አብይ ታላቅ ወንድም አቶ አበበ ጋሹ ጀግና፣ ለዓላማው የቆረጠ ወንድም ነበር ሲሉ ተናግረዋል።

ወንድሜን በማጣቴ መሪር ሀዘን ቢሰማኝም የተሰጠው እውቅና ሀዘኔ እንዳይበረታ አድርጎታልም ነው ያሉት።

የሻለቃ አብይ ጓደኛ ሃምሳ አለቃ አገኘሁ በዙ ደግሞ በውትድርና ዓለም ለረጅም ጊዜ አብረው መስራታቸውን ገልጾ ለሰንደቅ ዓላማው ፍቅር ያለው መሆኑንና ጀግንነቱን በተግባር ያስመሰከረ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም