በዓለም አራት ሚሊየን ስደተኛ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው-የተባበሩት መንግስታት

86
ነሃሴ 23/2010 አራት ሚሊየን ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ገልጿል። ኮሚሽኑ ባካሄደው ጥናት በዓለም የስደተኞች ቁጥር በመበራከት ትምህርት የማያገኙት ስደተኛ ህጻናት ቁጥር በአሳሳቢ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ጠቁሟል። በአንድ ዓመት ብቻ ከዚህ ቀደም ከትምህርት ገበታ ርቀው ከነበሩት ስደተኛ ህጻናት ቁጥር በግማሽ ሚሊየን የሚልቁ ህጻናት አሁንም ትምህርት እንዳማያገኙ ነው ያስታወቀው። በፈረንጆቹ 2017 መጨረሻ ከ25 ነጥብ 4 ሚሊየን የሚልቁ ስደተኞች በመላው ዓለም መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 19 ነጥብ 9 ሚሊየን ያህሉ በስደተኛ ኮሚሽኑ ስር ታቅፈዋል። ከ52 በመቶ የማያንሱት ስደተኞችም ህጻናት ሲሆኑ 7 ነጥብ 4 ሚሊየን ያህሉ እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ናቸው ተብሏል። ትምህርት ለህጻናት ወሳኝና ሀገራቸውን መልሰው ለመገንባትም ያግዛቸዋል ያሉት የስደተኞች ኮሚሽነር ፊሊፒዮ ግራንዲ፥ ያለ ትምህርት የህጻናቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ እና ማህበረሰቡ ላይ የህልውና አደጋ ላይ ይወድቃል ነው ያሉት። በዓለም ላይ 92 በመቶ ህጻናት በትምህርት ላይ ቢሆኑም ከስደተኛ ህጻናቱ ውስጥ ግን በትምህርት ገበታ ላይ የሚገኙት 61 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ህጻናቱ እድሜያቸው እየጨመረ በሄደ ቁጥረ ሁለተኛ ደረጃ የሚገቡት ቁጥራቸው እየቀነሰ እንደሚሄድም በጥናቱ ተመላክቷል። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ካገኙት ህጻናት ውስጥ ሁለት ሶስተኛ ያህሉ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አያገኙም፤ በአጠቃላይ በዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያገኙት 82 በመቶ ያህል ሲሆኑ ከስደተኛዎቹ ውስጥ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚያገኙት ግን 23 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የከፍተኛ ትምህርት የሚያገኙት ደግሞ ሽፋኑ 37 በመቶ ሲሆኑ ከስደተኛ ተማሪዎች ውስጥ የከፍተኛ ትምህርት የሚያገኙት አንድ በመቶ ብቻ ናቸው ተብሏል። በመሆኑም የትምህርት መሰረተ ልማት ላይ ያነጣጠሩ አፋጣኝ እርምጃዎች ካልተወሰዱ ሁኔታዎች እየባሱ እንደሚሄዱ ኮሚሽነር ግራንዲ ተናግረዋል። ምንጭ፦www.unhcr.or
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም