በአፋር በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የመድሀኒትና የህክምና መሳሪያ ድጋፍ ተደረገ

96

ሰመራ ጥር 8 ቀን 2014-(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያና የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በአፋር ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰባቸው ጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ ከ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የሕክምና መሳሪያዎችና መድሀኒቶች ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን ሃቢብ ናቸው።

የቢሮው ሀላፊ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ የጤና መሠረተ ልማቶችን መልሶ ወደሥራ ለማስገባት የክልሉ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው።

"የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያና የጽንስና ማህጸን ሃኪሞች ማህበር ያደረጉት ድጋፍ  በአሸባሪው ጉዳት የደረሰባቸው ጤና ተቋማትን ወደሥራ ለማስገባት እየተደረገ ላለው ጥረት አቅም ይሆናል" ብለዋል።

አቶ ያሲን እንዳሉት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድርና የሐረሪ ክልል ተቋማቱን ወደሥራ ለማስገባት ትልቁን ድርሻ ወስደው ድጋፍ አድርገዋል።

ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ አጋር አካላትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ነው የተናገሩት።

ለተደረገው የመድሃኒትና የህክምና ቁሶች ድጋፍ በክልሉ መንግስትና በተጎጂዎች ስም አመስግነው ዳያስፖራውና የተራድኦ ድርጅቶችም ለተጎጂዎች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታሁን ሃብቴ በበኩላቸው ድርጅቱ ከዚህ በፊት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና ቁሳቁስና መድሃኒት መደገፉን አስታውሰዋል።

ዛሬም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የተለያዩ መድሃኒቶችን ለሁለተኛ ጊዜ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው "ድርጅቱ በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።  

ሌላው ድጋፍ ያደረገው የኢትዮጵያ ጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ዘነበ አካሉ በበኩላቸው የሙያ ማህበሩ የተለያዩ መድሃኒትና ለማዋለጃ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ የህክምና ቁሶችን ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ማህበሩ ያደረገው ድጋፍ ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት ተናግረዋል።

በቀጣይም የክልሉን ክፍተት መሰረት በማድረግ ማህበሩ መድሃኒትና ተያያዥ የህክምና ግብአቶችን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም