አሸባሪው የህወሃት ቡድን ቅርሶችን ከማውደሙ ባሻገር የቅርስ ጥገና ስራዎችን አስተጓጉሏል

209

አዲስ አበባ፣ ጥር 07/2014(ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ቅርሶች ላይ ውድመትና ዝርፊያ ከመፈጸሙ ባሻገር የቅርስ ጥገና ስራዎችን እንዳስተጓጎለ የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የሽብር ቡድኑ በተለይ በደቡብ ጎንደር፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ወሎና ሰሜን ሸዋ አካባቢዎች ባሉ ቅርሶች ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳትና ዝርፊያ መፈፀሙ በጥናት ተረጋግጧል።

የሽብር ቡድኑ በእነዚህ አካባቢዎች በሚገኙ ቋሚ ቅርሶች ላይ ውድመት እንዲሁም ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ላይ ደግሞ ዘረፋ መፈጸሙን ነው የተናገሩት፡፡

በተለይም በእምነት ተቋማት በሚገኙ ቅርሶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደፈጸመ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በቆዩ አካባቢዎች በቅርሶች ላይ ከፈጸመው ውድመትና ዝርፊያ ባሻገር የቅርስ ጥገና ስራዎችን ማስተጓጎሉንም ነው የተናገሩት፡፡

ለአብነትም በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት የላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት ጥገና ሂደት በወቅቱ እንዳይጀመር አድርጓል ነው ያሉት፡፡

አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት ምክንያት የጥገና ባለሙያዎችን ከፈረንሳይ አስመጥቶ ስራውን ለመስራት እክል መፍጠሩንም አብራርተዋል።

በዚህም በላልይበላ አብያተ ክርስቲያናት በአስቸኳይ መከናወን ያለባቸው 24 የጥገና ስራዎች እንዳልተጀመሩ በመጥቀስ፡፡

በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ምክንያት የተጎዱ ቅርሶችን የመጠገኑ ስራ አስፈላጊው ጥናት ተደርጎ ከአማራ ክልል ጋር በቅንጅት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

ባለስልጣኑ በአሁኑ ወቅት የተዘረፉ ቅርሶችን የሚመለከት ዝርዝር ጥናት እያከናወነ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡