በጎንደር ከተማ ሃገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር ተከፈተ

ጎንደር ፤ ጥር 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጎንደር ከተማ ከ280 በላይ የሃገር ውስጥና የውጭ አምራቾችና ድርጅቶች የተሳተፉበት ሃገር አቀፍ የንግድ ትርኢትና ባዛር ዛሬ ተከፈተ።

በመክፈቻ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ የከተማዋ አስተዳደር ንግድ መምሪያ ሃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ፀጋዬ እንዳሉት፤ የንግድ ትርኢትና በዛሩ የጎንደር ከተማን የንግድና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

በዝግጅቱ ከ80 በላይ የውጭና ከ200 በላይ የሃገር ውስጥ አምራቾች እንዲሁም አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችና ነጋዴዎች ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የንግድ ትርኢትና በዛሩ ለ10 ቀናት ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ አመልክተው፤ ከዝግጅቱ ከሚገኘው ገቢም 25 በመቶ ለዘማች ቤተሰቦች ድጋፍ የሚውል መሆኑን ገልጸዋል።

''አምራችና ሸማቹን በማገናኘት የጎንደር ከተማን የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ ነው'' ያሉት ደግሞ የከተማዋ አሰተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ ናቸው።

ዝግጅቱ በወርሃ ጥር በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ልዩ የበዓል ድባብ የሚፈጥር ከመሆኑም በላይ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ለማጠናከር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ የመጡት አቶ ኢብራሄም ሷሊህ በሰጡት አስተያየት፤ የጎንደር ከተማ አስተዳደር ንግድና ትርኢት ማዘጋጀት በመቻሉ የንግድ እቃዎችን ለመሸጥ በዝግጅቱ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

ከደቡብ ክልል የመጡት አቶ ሂርፔሳ ዳቻሳ በበኩላቸው፤ የከተማው ህዝብ እንግዳ ተቀባይና አክባሪ መሆኑን ጠቅሰው፤በዝግጅቱ የእንጨት ስራ ውጤቶችን ለመሸጥ ይዘው መምጣታቸውን ተናግርዋል።

የንግድ ትርኢትና ባዛሩን ከ600 ሺህ በላይ የከተማውና አካባቢው ህዝብ ይጎበኘዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም