በአሸባሪው ህወሓት ለተጎዱ የደሴ ከተማ ነዋሪዎች የ3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ተደረገ

100

ደሴና ደብረ ብርሃን ፣ ጥር 7/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶሱ በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የምግብ እህልና ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ አደረገ፡፡

በተመሳሳይ ቤተክርስቲያኗ የቴክሳስና አካባቢዋ ሀገረ ስብከት የዳላስ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት በጦርነቱ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደርጓል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤት ክርስቲያን የስብከት ወንጌል መምሪያ ሊቀ ጳጳስና የሲኖዶሱ ተወካይ ቅዱስ አቡነ ማርቆስ  እንደገለጹት የገጠመንን ሁለንተናዊ ችግር ተጋግዘንና ተረዳድተን እናልፈዋለን።

የኢትዮጵያውያን የአንድነት፣ አብሮነትና የሰላም እሴት በማስቀጠል አንዱ ለሌላው አካፍሎ መብላትና መጠጣት እንዳለብትም አስገንዝበዋል።

ዳግም እንዲህ ዓይነት ችግር እንዳይከሰትና የሰው ደም እንዳይፈስ ሁሉም በእየምነቱ መፀለይና ይበቃል እያለ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማስተማር ኃላፊነቱን እንዲወጣም አሳስበዋል፡፡

ፈጣሪ ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ሲሉ በየተራራውና በየሸለቆው ለተሰውት ምህረትን፣ ለቆሰሉት ማገገምን በስራ ላይ ላሉትም ብርታትን እንዲሰጣቸው ሁሉም መፀለይና ማገዝ ይኖርበታል፡፡

በደሴ ከተማ በሽብር ቡድኑ ለተጎዱና ለተቸገሩ ዜጎች የሚሆን ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የምግብ እህልና ጥሬ ገንዘብ ዛሬ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤት ክርስቲያን የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ መምህር ዳንኤል ሰይፈሚካኤል በበኩላቸው የተደረገው ድጋፍ 400 ኩንታል ዱቄትና ጥሬ ገንዘብ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለሰሜን ወሎና ለዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞኖችም ተመሳሳይ ድጋፍ መላኩን ጠቁመው፤ ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግም እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በጦርነቱ የተጎዱ ተቋማትንና ዜጎችን መልሶ ለማቋቋምና ሰብዓዊ የእለት ደራሽ ምግብ ለማድረግም ቤተ ክርስቲያኗ ኮሚቴ አቋቁማ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አትናቲዎስ በበኩላቸው ቤተክርስቲያኗ ያደረገችው ድጋፍ የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል፡፡

የገጠመንን ችግር በጋራ አልፈን የምንማርበት፣ አንድነታችን የምናጠናክርበትና ሀገራችንን በዘላቂነት የምንጠብቅበት መሆን አለበትም ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ ሰለሞን ጋሻው በበኩላቸው በአሸባሪው የትግራይ ወራሪ ኃይል ለችግር የተጋለጡና ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ከ320 ሺህ እንደሚበልጡ ጠቅሰዋል።

ተወካዩ እንዳሉት መንግሥት ተቋማትን፣ ኅብረተሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ ለማድረግ እየሰራ፤ በዘላቂነት መልሰው እንዲቋቋሙም በቅንጅት እየተሰራ ነው፡፡

በሌላ በኩል በቤተክርስቲያኗ በቴክሳስና አካባቢዋ ሀገረ ስብከት የዳላስ ቤተ ክህነት ጽህፈት ቤት  በሰሜን ሸዋ ዞን በሽብር ቡድኑ ለጉዳት ለተጋለጡ ወገኖች የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ተናግረዋል።

በአሸባሪው ቡድን የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም በውጭ የሚኖሩ አትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እየሰሩ ነው ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳደሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ በበኩላቸው የህውሓትና የሸኔ አጥፊ ቡድኖች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቢያሴሩም የኢትዮጵያ ህዝብ ባደረገው ተጋድሎ ሴራቸው መክሸፉን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኖቹ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ጠቅሰው፤ ከችግሩ ግዝፈት አንፃር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም