አገራዊ ምክክሩ የተረጋጋችና ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማሸጋገር ሚናው የጎላ ነው

217

ጥር 07 ቀን 2014 (ኢዜአ) አገራዊ ምክክሩ የተረጋጋችና ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማሸጋገር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው የአዲስ አበባ ወጣቶች ማሕበር ገለፀ።

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበትም ነው ማህበሩ ጥሪ ያቀረበው፡፡

የማህበሩ ዋና ጸሃፊ ወጣት ይሁነኝ መሐመድ ከኢዜአ ጋር በነበረው ቆይታ በኢትዮጵያ በሚከሰቱ አዎንታዊ ተግባራት ቀዳሚ ተጠቃሚዎች ወጣቶች መሆናቸውን ነው የገለጸው፡፡

ግጭትና አለመረጋገቶች ሲከሰቱም ወጣቶች ይበልጥ ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጾ፤ ከዚህ አኳያ የትኛውም አይነት አለመግባባት በውይይትና ምክክር ሊፈቱታ ይገባል ነው ያለው፡፡

በመሆኑም በአሁኑ ወቅት  በኢትዮጵያ ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክር ወጣቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡

አገራዊ ምክክሩ የተረጋጋችና ሰላሟ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ ለማሸጋገር ጉልህ ሚና እንደሚኖረውም ነው ያብራራው፡፡

አገራዊ ምክክሩ ለረዥም ጊዜ ሲከባለሉ የመጡ አለመግባባቶችን በመፍታት የተሻለች ኢትዮጵያን  ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ተናግሯል፡፡

ችግሮችን በምክክርና ውይይት አለመፍታት ኢትዮጵያን ለከፋ ቀውስ እንደሚያጋልጣት የሚናገረው ዋና ፀሐፊው፤ በመሆኑም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለበት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የተለያዩ ሴራዎችን በመሸረብ አገራዊ ምክክሩ እንዳይሳካ የሚሰሩ አካላት ደግሞ የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት የማይፈልጉ መሆናቸው በግልጽ ሊታወቅ ይገባል ነው ያለው፡፡

እነዚህ አካላትን ሴራ በማጋለጥ ረገድ በጋራ መስራት እንደሚገባም ተናግሯል፡፡

ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት በተለይ ወጣቶች ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገንዝበው የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባም የማህበሩ ዋና ጸሃፊ ወጣት ይሁነኝ መሐመድ መልእክት አስተላልፏል፡፡