ጦርነቱን በጠንካራ አንድነት በማሸነፍ ያገኘነውን ድል በልማቱም ልንደግመው ይገባል

180

ባህር ዳር፣  ጥር 7/2014 (ኢዜአ) ”አሸባሪው ህወሓት የለኮሰውን ጦርነት በጠንካራ አንድነት በማሸነፍ ያገኘነውን ድል በልማቱም በመድገም ከድህነት ልንወጣ ይገባል” ሲሉ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር እያሱ ኤልያስ ገለፁ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን መታቀዱም ተመላክቷል።

የአማራ ክልል የበጋ ወራት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ዛሬ በክልል ደረጃ በደቡብ ጎንደር ዞን ሊቦ ከምከም ወረዳ ተጀምሯል።

ሚኒስትር ዴኤታው በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ እንዳሉት በአሸባሪው ህወሓት የተቃጣውን ጦርነት ለመቀልበስ ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሏል።

“ለም መሬት ይዘን በሚፈለገው ልክ መስራት ባለመቻላችን ስንዴ መለመን ያሳፍራል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የደን መመናመን፣ የአየር ንብረት ለውጥና የአፈር መሸርሸርን መከላከል የሚቻለው የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራውን በጦርነቱ ውጤታማ ለመሆን ከተሰራው ባላነሰ አጠናክሮ መስራት ሲቻል መሆኑን አስታውቀዋል።

ፕሮፌሰር እያሱ እንዳሉት በዘንድሮው የበጋ ወራት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ ለማከናወን ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።

እንደ እሳቸው ገለጻ የሚገነቡ ግዙፍ ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ ለማድረግና ለአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 6 ቢሊዮን ችግኝ እየተዘጋጀ ነው።

አሸባሪና ወራሪውን የህወሓት ቡድን በመመከት በጦርነቱ ያገኘነውን ድል በልማቱ ለመድገም ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጠንክረን ልንሰራ ይገባል ሲሉም ፕሮፌሰር እያሱ ጥሪ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ጌታቸው ጀምበር በበኩላቸው “አሸባሪው ህወሓት ክልላችንን በመውረር በዜጎቻችን ላይ የከፋ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል” ብለዋል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ ዓልሞ የተነሳውን አሸባሪ ቡድን መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች በከፈሉት መስዋዕትነት ቡድኑ እርምጃ ተወስዶበት ከወረራቸው አካባቢዎች በሀይል እንዲወጣ መደረጉን ገልጸዋል።

“አሸባሪው ህወሓት እንደገና ተደራጅቶ ትንኮሳ እንዳይፈጽም የአማራ ህዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ተዘጋጅቶ ክልሉንና ሀገሩን ሊጠብቅ ይገባል” ብለዋል።

የክልሉን ልማት በማፋጠን በወራሪው ቡድን የታጣውን ምርት ለማካካስ በትኩረት መስራት እንደሚገባም ዶክተር ጌታቸው አስገንዝበዋል።

“የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራ አንዱ የልማት አውደ ውጊያ በመሆኑን ጠንክረን መስራት ይኖርብናል” ሲሉም አሳስበዋል።

ለዚህም መላ አርሶ አደሩ፣ በየደረጃው የሚገኘው አመራር፣ የግብርና ባለሙያ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራውን በማጠናከር የጥፋት ኃይሎችን አንገት ማስደፋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራን በመስራት የአፈር ለምነትን ለማሻሻልና ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉም ሌት ተቀን እንዲሰራም አሳስበዋል።

በዘንድሮው የበጋ ወራት በክልሉ ከ8 ሺህ በሚበልጡ ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ እንደሚከናወን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው ናቸው።

በነዚህ ተፋሰሶች ውስጥ የአካባቢውን የመሬት አቀማመጥ መሰረት ያደረጉ የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎች እንደሚከናወኑም ገልፀዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ወራት በሚካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራም ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ።

ዛሬ በተካሄደው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ማስጀመሪያ መርሀግብር ላይ የክልል፣ የፌዴራልና የዞን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል።