ድርጅቱ በ171 ሚሊዮን ብር ወጭ የመኖሪያና የንግድ አፓርትመንቶችን እያስገነባ ነው

170

ጎንደር፣ጥር 7/2014 ዓ.ም(ኢዜአ)የአማራ ቤቶች ልማት ድርጅት በክልሉ በሚገኙ ከተሞች በ171 ሚሊዮን ብር ወጭ የመኖሪያና የንግድ አፓርትመንቶችን እያስገነባ መሆኑን አስታወቀ።

ድርጅቱ በጎንደር ከተማ በ28 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባውን ባለ ስድስት ወለል የንግድ አፓርታማ ሕንፃ ዛሬ አስመርቋል።

የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ አቶ አበረ ሙጨ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ እንዳሉት ድርጅቱ በክልሉ በዋና ዋና ከተሞች የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል ጥረት እያደረገ ነው።

ለዚህም በባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ደሴና ወልዲያ ከተሞች የመኖሪያና የንግድ አፓርታማ ሕንፃዎችን ግንባታ እያካሄደ ይገኛል ብለዋል።

በባህር ዳር፣ ደሴና ወልዲያ ከተሞች ከሰባት እስከ ዘጠኝ የወለል ከፍታ ያላቸው ስድስት የመኖሪያና የንግድ አፓርታማ ሕንፃዎች ግንባታ እያስገነባ መሆኑን አስረድተዋል።

በጎንደር ዛሬ ከተመረቀው ውጭ ባለ 13 ወለል የመኖሪያና የንግድ አፓርታማ በ80 ሚሊዮን ብር ወጭ ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችል የዲዛይን ስራ መጠናቀቁንም ገልፀዋል።

አሸባሪው ህወሓት በምስራቅ አማራ በፈፀመው ወረራ በወልዲያ፣ ደሴና ኮምቦልቻ በሚገኙ የድርጅቱ ሕንፃዎች ላይ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ዘረፋና ውድመት መፈጸሙን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በወረራው ሳቢያ ድርጅቱ ለንግድና መኖሪያ ቤት ከተከራይ ደንበኞች ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ወርሃዊ ኪራይ መሰብሰብ እንዳልቻለ አመልክተዋል።

ድርጅቱ ወቅታዊ ችግሮችን ተቋቁሞ በከተሞች የሚስተዋለውን የንግድና መኖሪያ ቤት አፓርታማ እጥረት ለመፍታት እያደርገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በጎንደር ዛሬ የተመረቀው ባለ ስድስት ወለል ሕንፃ የንግድ ሱቆችን ጨምሮ ለልዩ ልዩ አገልግሎት የሚውሉ 83 ቤቶች እንዳሉት በድርጅቱ የጎንደር ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሁንልኝ ገልጸዋል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው ድርጀቱ በከተማው የሚታየውን የመኖሪያ ቤት እጥረት ለማቃለል እያከናወነ ያለው የልማት ስራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

በጦርነት ቀጠና ውስጥ ሆኖ ልማት ማካሄድ እንደሚቻል የድርጅቱ የሕንፃ ግንባታ ማሳያ መሆኑንም  ጠቅሰዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው የቤት ልማት ፕሮጀክቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ የክልል፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ የንግዱ ማህበረሰብና ጥሪ የተደረገላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የአማራ ቤቶች ልማት ድርጅት በክልሉ በሚገኙ 11 ከተሞች 3 ሺህ 700 ቤቶችን እያስተዳደረ ይገኛል።