አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ውደመትና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙን ተመልክቻለሁ

56

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2014 ( ኢዜአ)  አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች ከፍተኛ ውደመትና ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት መፈጸሙን እንደታዘበ በደቡብ አፍሪካ ሶዌቶ የወጣቶች እንቅስቃሴ መሪ ሎንታታ ላክስ ገለጸ።

በኢትዮጵያ ቆይታው አንዳንድ የምእራባዊያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያስተላልፉት መረጃና መሬት ላይ ያለው ሃቅ የተለያየ መሆኑን እንዳረጋገጠም ነው የተናገረው፡፡

በደቡብ አፍሪካ ሶዌቶ የወጣቶች እንቅስቃሴ መሪ ሎንታታ ላክስ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ የጋሸናና ላልይበላ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ ጎብኝቷል፡፡

በዚህም የሽብር ቡድኑ በርካታ የመሰረተ ልማቶችን ማውደሙንና ከፍተኛ ኢ-ሰብዓዊ ደርጊት መፈጸሙን እንደታዘበ ገልጾ፤ ቡድኑ አውዳሚ ባህሪ ያለው መሆኑን ተናግሯል።

በተለይም ንጹሃን ዜጎችን ጨፍጭፎ በጅምላ መቅበሩንና ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር ከፍተኛ ግፍ እንደፈጸመም ነው የተናገረው፡፡

ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የህዝብ መገልገያ ተቋማት ላይ ውድመት መፈጸሙንም እንዲሁ፡፡

ነገር ግን አንዳንድ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን በተመለከተ የሐሰት መረጃና ፕሮፓጋንዳ እያሰራጩ መሆናቸውን አብራርቷል።

በኢትዮጵያ ቆይታው አንዳንድ የምእራባዊያን ሚዲያዎች ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚያስተላልፉት መረጃና መሬት ላይ ያለው ሃቅ የተለያየ መሆኑን እንዳረጋገጠም ተናግሯል፡፡

በኢትዮጵያ ሕዝብና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል ጠንካራ አጋርነት መኖሩን እንደተመለከተም ነው የሚገልጸው፡፡     

በኢትዮጵያ ላይ ተገቢ ያልሆነ የውጭ ጫና እየተደረገ መሆኑን ገልጾ፤ ይህን በመመከት ረገድ አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያ ጎን መቆም እንዳለባቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡  

አፍሪካውያን በአንድነት በመቆም የምዕራብ አገራትን ጫና መመከት እንዳለባቸውም ጠቁሟል።

ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚሰሩት የውስጥ ሃይሎችን የሚደግፉ የውጭ ሃይሎች መኖራቸውን መረጃዎች እንደሚያሳዩ ገልጾ፤ እነዚህ አካላት ከኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ማንሳት እንዳለባቸው ተናግሯል፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ወጣቶች አገርን ሊጠቅም የሚችል አጀንዳ ላይ በመሳተፍ ለአገራቸው አዎንታዊ ሚና መጫወት እንዳለባቸውም መክሯል፡፡

ወጣቶቹ በአገራዊ ጉዳይ ላይ በጋራ መሰለፍ እንዳለባቸውና በወጣቶች የሚነሱ ጠቃሚ አገራዊ አጀንዳዎች ተደማጭ እንዲሆኑ መሥራት እንደሚገባም እንዲሁ፡፡   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም