ዳያስፖራው ማህበረሰብ በወራሪው ኃይል ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

61

ባህር ዳር ጥር 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዳያስፖራው ማህበረሰብ በአሸባሪው ህወሓት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋምና ኢኮኖሚው እንዲያገግም እየተደረገ ላለው ጥረት የድርሻቸውን እንዲወጡ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ።

በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት የተዘጋጀው የዳያስፖራ ማህበረሰብ የትብብር ሲምፖዚየም በባህር ዳር እየተካሄደ ነው።ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በሲፖዚየሙ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት አሸባሪው ህወሓት በወረራ ከያዛቸው ዞኖች እንዲወጣ የተደረገው በመላው የአትዮጵያ ህዝብ ትብብር ነው።የመከላከያ ሰራዊታችን፣ ልዩ ሃይሎች፣ ሚሊሻዎችና ሌሎች የጸጥታ አካላት በግንባር ባካሄዱት ተጋድሎ ጠላትን መመከት መቻሉንም ገልፀዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ዳያስፖራውና ሌሎች የሀገራችን ወዳጆች ያበረከቱት አስተዋፅኦ የሚበረታታና መቀጠል ያለበት ነው ብለዋል።

በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሁም ውዳጆች የተዛባውን የአንዳንድ መንግሥታትን የዲፕሎማሲ እይታ ለማስተካከል የዕለት ኑሯቸውን ወደ ጎን በመተው በ'No More!' እንቅስቃሴ ያሳያዩት ትብብር ሲታውስ የሚኖር አኩሪ ታሪክ መሆኑን ገልፀዋል።የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት ቀደም ሲል የጀመሩትን ጠንካራ ድጋፍ አሁንም በመልሶ ግንባታውና በጦርነቱ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማቋቋም እየተደረገ ላለው ጥረት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።

እንዲሁም በአዋጭ ኢንቨስትመንት መስኮች በመሳተፍ ክልሉ ካለበት የኢኮኖሚ ችግር ፈጥኖ እንዲወጣ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

"ከተባብርን እና አብረን የመስራት አጋጣሚዎችን በአግባቡ ከተጠቀምን አሁን የገጠመንን ጠላት ከማሸነፍ ባሻገር የማይደፈር ክልልና ሀገር መገንባት እንችላለን" ሲሉም ዶክተር ይልቃል ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ሕልውናን ለማስጠበቅ የመጀመሪያው ተግባር የውስጥ አንድነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን በበኩላቸው ወራሪውን ሀይል በመመከት ሁሉም ህዝባችን የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል።

አቶ ስዩም እንዳሉት በዋግ ኽምራ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደር፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ፣ እንዲሁም በደቡብና ሰሜን ጎንደር የሚገኙ የፀጥታ መዋቅሮች ከጠላት ጋር በመፋለም ለተገኘው ድል መሰረት ሆነዋል።

አሁንም ጦርነቱ ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ በመሆኑ የሕዝቡንና የዳያስፖራውን ማህበረሰብ ትብብር የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

በክልሉ መንግሥት በተዘጋጀው የዳያስፖራ የትብብር ሲምፖዚየም ላይ የክልሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የዳያስፖራው ማህበረሰብ አባላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም