ኢንስቲትዩቱ በኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እና ኪነ-ጥበብ ላይ ጥናትና ምርምር እያካሄደ ነው

223

አዲስ አበባ፣ ጥር 7/2014 ( ኢዜአ) የኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እና ኪነ-ጥበብን ለማሳደግ የጥናትና ምርምር ስራ እያከናወነ መሆኑን የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡

በኢንስቲትዩቱ የኦሮሞ ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ማሞ ሰቦክሳ እየተካሄዱ ስላሉት አራት የጥናትና ምርምር ስራዎች ለኢዜአ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ከአራቱ የጥናትና ምርምር ስራዎች መካከል ሁለቱ ተጠናቀው በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡  

በኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክ እና ኪነ-ጥበብ ላይ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ለሕዝብ ከማስተዋወቅ ባሻገር ለአዲሱ ትውልድም ይተላለፋሉ ብለዋል፡፡

የጥናትና ምርምር ስራዎቹ የኦሮሞን ባህልና ማንነት ትክክለኛ ስዕል የሚያስተዋውቁ ከመሆናቸውም በላይ የባህል እውቀትን የሚያስፋፉ እንደሆኑም ገልጸዋል።

የባህል እውቅት መስፋፋት ደግሞ አንዱ ስለ ሌላው የማወቅ፣ የመጋራትና እርስ በእርስ የመተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር በመሆኑ በሠላም አብሮ የመኖር እሴትን የሚያጎለብት ይሆናል ነው ያሉት።

ኢንስቲትዩቱ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ከተለያዩ ባለ ድርሻ አካላት ጋር እየሰራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባና የጅማ ዩኒቨርሲቲዎች ራሱን የቻለ የኦሮሞ ጥናት ኢንስቲትዩት ስላላቸው በጋራ መስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ መፈራረምና የረጅም ጊዜ የስትራቴጂክ ዕቅድ ማዘጋጀት ችለናል ብለዋል።

ከዩኒቨርሲቲዎቹ በተጨማሪም በአገር ውስጥ ከተለያዩ የባህል ማዕከላትና ተቋማት፣ በውጭ አገራት ደግሞ ከጀርመንና ከኢጣሊያ የባህል ማዕከላት ጋር የስራ ግንኙነት ለመፍጠር መታቀዱን አክለዋል።

ኢንስቲትዩቱ ከኦሮሞ ባህል ማዕከል በመውጣት ራሱን ችሎ ከተቋቋመ አንድ ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህልና ኪነ-ጥበብ ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል፡፡

የኦሮሞ ባህል ማዕከል ደግሞ የቤተ መጻሃፍት፣ የሙዚየም እና የቤተ መዘክር አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል።