በአሸባሪው ህወሓት ወረራ የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለመገንባት የሚያግዝ ሲምፖዚየም ሊካሄድ ነው

72

ባህር ዳር፣ ጥር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ለመገንባት የሚያግዝ የዳያስፖራ ትብብር ሲምፖዚየም ነገ በባህርዳር ከተማ እንደሚካሄድ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ ዛሬ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ  ሲምፖዚየሙ በክልሉ በአሸባሪው ህወሓት የደረሰውን ጉዳት በማስገንዘብ የዳያስፖራው ማህበረሰብ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ የሚያስችል ነው።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ መንግሥት ባቀረበው ጥሪ መሰረት ከገና በዓል ጀምሮ በክልሉ የሚከበሩ ህዝባዊና ሃይማኖታዊ በዓላትን በመታደም የቱሪዝም ዘርፉ እንዲነቃቃ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በአሸባሪው ቡድን የደረሰውን ሰብዓዊ ጉዳትና ቁሳዊ ውድመት በአካል ተገኝተው እንዲመለከቱ መደረጉን ገልጸዋል።

በመልሶ ግንባታው አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ሲምፖዚየሙ እንደሚያግዝ አመልክተዋል።

በሲምፖዚየሙ ላይ በደረሰውን የጉዳት መጠን ላይ ትኩረት ያደረጉ የውይይት ሃሳቦች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል።

በክልሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስተዋወቅ ዳያስፖራው ሀብቱን፣ እውቀቱንና ክህሎቱን ለሀገሩ እንዲያውል መነሳሳትን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

ነገ ምሽት ለዳያስፖራው ማህበረሰብ የአንድነትና የትብብር ማዕድ ግብዣ እንደሚደረግ ጠቁመው፤ ለተጎዱ ወገኖች መልሶ ለማቋቋም ያለመ የገቢ ማሰባሰብ ይካሄዳልም ብለዋል።

የጥምቀትን በዓል በጎንደር ከተማ በደማቅ ሁኔታ ለማክበር ሰፊ ዝግጅት መደረጉን የጠቆሙት የቢሮው ሃላፊ ዳያስፖራው የበዓሉ ተካፋይ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም