በእስር ላይ የነበሩ የተወሰኑ ግለሰቦች ክስ መቋረጡ ለሀገራዊ ምክክሩ ስኬት አስተዋጽኦ ይኖረዋል

172

መቱ፣ ጥር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስት በተለያየ ወንጀል ተጠርጥረው በእስር ላይ የነበሩ የተወሰኑ ግለሰቦች ክስ እንዲቋረጥ መወሰኑ ለብሔራዊ ምክክሩ ስኬት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የህግ ባለሙያዎች ገለጹ።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ በኢሉባቦር ዞን የሚገኙ የሕግ ባለሙያዎቹ እንዳሉት፤ በቀጣይ ለሀገር ግንባታም ሆነ ለዜጎቿ አንድነትና ተጠቃሚነት በሚበጁ ጉዳዮች ላይ መስራት ያስፈልጋል።

የኢሉባቦር ዞን አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ሁንዴ ተፈራ እንደገለጹት፤ የሀገሪቱን የሕግ መሰረት አድርጎ በእስር ላይ የነበሩ የተወሰኑ ግለሰቦችን ክስ የማቋረጥ ውሳኔ ትልቅ ጠቀሜታ አለው።

የውሳኔው አንድምታ ለዘላቂ ሀገራዊ ሰላም፣ ልማትና ዕድገት መረጋገጥ እንዲሁም ለአንድነትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

በመንግሥት ውሳኔ ክሳቸው የተቋረጠላቸው ግለሰቦች ሀገርና ሕዝብን አስቀድመው መስራት የሚችሉበትን ዕድል እንዳገኙ የጠቆሙት ደግሞ ሌላው የሕግ ባለሙያ  አቶ ዓዲሳለም ቀኖ ናቸው።

ሕዝባዊ ፋይዳና ሀገራዊ ጠቀሜታ እንደሚኖራቸው ከታመነበት በሕግ ተይዘው በክርክር ሂደት ላይ የሚገኙ ጉዳዮችን ማቋረጥ እንደሚቻል በአዋጅ ተደንግጎ እንደሚገኝም አስታውሰዋል።

የውሳኔው የኋላ መሰረትም ሕዝባዊ ተጠቃሚነትና ሀገራዊ አንድነትን ለመገንባት መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ሀገር የምትለወጠውና ወደፊት መራመድ የምትችለው በውይይትና በምክክር መሆኑን ገለጸው፤ ለሀገር የሚጠቅሙትን በመውሰድና በመደጋገፍ ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥና ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማዋል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 መሠረት የወንጀል ምርመራ መዝገብን የማቋረጥና የመዝጋት፣ የክስ መዝገብን የማቋረጥ አሠራር ሥርዓትን ለመደንገግ  የወጣ መመሪያ ቁጥር 3/2012 ያመለክታል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼