ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው

212

አዲስ አበባ፣ ጥር 06/2014 (ኢዜአ) ሀገራዊ የምክክር መድረኩ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይኖረዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ዳያስፖራዎች ገለጹ።

ዳያስፖራዎቹ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ ምክክሩ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቱ የሚታየውን ወጥነት የሌለው አረዳድ ወደ አንድ ለማምጣት ያስችላል።

ይህም ሀገሪቷን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ነው ያነሱት።

ከአሜሪካ የመጡት ዶክተር አክሊሉ ምንይልሸዋ የጋራ አቋም ያልተያዘባቸው በርካታ የታሪክ ምዕራፎች የንትርክና የጭቅጭቅ ምንጭ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

“ይህም እርስ በእርስ ግራ እና ቀኝ በመሳሳብ ትኩረታችንን ልማት ላይ እንዳናደርግና ከድህነት እንዳንወጣ አድርጎናል” ነው ያሉት።

በመሆኑም የምክክር መድረኩ የተዛባውን የታሪክ አረዳድ በማረምና ብሔራዊ መግባባት በመፍጠር ለጋራ አላማ በጋራ ለመሰለፍ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለው ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር መድረኩ የተዛቡ የታሪክ ምልከታዎችን ለማረም ያስችላል ያሉት ደግሞ ከአሜሪካ የመጡት ፓስተር እስራዔል ገበየሁ ናቸው።

በሀገሪቱ ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ አስተዋጽኦው የጎላ እንደሚሆንም አንስተዋል።

ምክክሩ ግቡን እንዲመታ በውይይቱ የሚሳተፉ አካላት ከግል ፍላጎታቸው ወጥተው ሀገርን የሚጠቅም ሥራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ዳያስፖራዎቹ ለሀገራዊ የምክክር መድረኩ ስኬት የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።