በምልክት ቋንቋና በብሬል የሚሰጠው “የአካቶ ትምህርት” ተደራሽነትን ለማስፋት 5 ሺህ ድጋፍ ሰጪ ማዕከላት ይገነባሉ

202

ጥር 06 2014 (ኢዜአ) በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በምልክት ቋንቋና በብሬል የሚሰጠው “የአካቶ ትምህርት” ተደራሽነትን ለማስፋት በአምስት ዓመት ውስጥ 5 ሺህ ድጋፍ ሰጪ ማዕከላት የመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ትምህርት ሚኒስቴር ገለጸ።

በአገሪቱ ከሚገኙ ከ45 ሺህ በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአካቶ ትምህርት የሚሰጡት ከአንድ ሺህ እንደማይበልጡም ተነግሯል።

“አካቶ ትምህርት” መስማት ለተሳናቸው የምልክት ቋንቋ፣ ማየት ለማይችሉ ደግሞ የብሬል ትምህርቶችን በመደበኛ ትምህርት ውስጥ በልዩ ፍላጎት ትምህርት አካቶ መስጠት ነው።

ፍቅር የኢትዮጵያ አዕምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር ያዘጋጀው በአካቶ ትምህርት ላይ ያተኮረ ውይይት ዛሬ ተካሂዷል።

በውይይቱ የትምህርት ሚኒስቴር የልዩ ድጋፍና አካቶ ትምህርት ዳይሬክተር አቶ ተክላይ ገብረሚካኤል በትምህርት ዘርፉ ችግሮች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በአገሪቷ በአዕምሮ ዕድገት ውስንነት ሳቢያ በርካታ ህፃናትና ወጣቶች ወደ ትምህርት ገበታ እንደማይመጡ፤  ቢመጡ እንኳን በቂ እውቀት የሚያገኙበት አሰራር አለመዘርጋቱን ተናግረው በአገሪቷ ከሚገኙ ከ45 ሺህ በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የአካቶ ትምህርት የሚሰጡት ከአንድ ሺህ እንደማይበልጡም ነው ያስረዱት።

ችግሩን ለመቅረፍ በመንግስት ስትራቴጂ ተነድፎ እየተተገበረ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ የአካቶ ትምህርት ድጋፍ መስጫ ማዕከላትን የመደገፍ፣ ስልጠና የመስጠትና ተዛማጅ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።

በስትራቴጂው በትምህርት ቤቶች ውስጥ የአካቶ ትምህርት ተደራሽነትን ለማስፋት በአምስት ዓመት 5 ሺህ ድጋፍ ሰጪ ማዕከላትን ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ጠቁመዋል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ ዳይሬክተር አቶ አሳልፈው አመዲን የአካቶ ትምህርት ጉዳይ ትኩረት የሚሻ መሆኑን አመልክተዋል።

የአካቶ ትምህርት የሚያስፈልጋቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚያካትት ስርዓት ለመዘርጋት ከተቋማት ጀምሮ የሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸው በተለይም በዚህ ጉዳይ ከወላጆች ጀምሮ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የተዛባ አመለካከት ሊቃና እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

ፍቅር የኢትዮጵያ አዕምሮ እድገት ውስንነት ብሔራዊ ማኅበር ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ምህረት ትንሳኤ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት የሚታይባቸው ዜጎች የትምህርት ዕድል ማግኘት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እነዚህ አካላት የተመቻቸ ሁኔታና ዕድል ካገኙ እንደማንኛውም ኅብረተሰብ አምራችና ንቁ ዜጋ ይሆናሉ ብለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት ይህን በመገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

ፕሬዚዳንቷ ብሔራዊ ማኅበሩ 70 ህጻናትን ይዞ የተለያዩ ስልጠናዎችና ትምህርቶች እንዲያገኙ እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአካቶ ትምህርትን አስመልክቶ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ምክክር ጥናታዊ ጹሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ከወጣው መርሃ ግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡