"አንድ ቤተሰብ መርዳት" በሚል መርህ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለማገዝ እንቅስቃሴ ጀምረናል

77

አዲስ አበባ፣ ጥር 06/2014(ኢዜአ) በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን "አንድ ቤተሰብ" መርዳት በሚል መርህ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገለጹ።

አሸባሪው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ ባደረገበት ወቅት የተጎዱ ዜጎችን ደግፎ ወደ ቀድሞ ህይወታቸው መመለስ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት መሆኑን በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተናግረዋል።

ነዋሪነታቸው በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የሆኑት ፓስተር ወርቅነህ ዘርፉ እና ወይዘሮ እልፍነሽ ሃይሌ ወቅቱ የአገር መውደድ በተግባር የሚተረጎምበት እንደሆነ ገልጸዋል።

"በተለይም ደግሞ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን እነዚህን ወገኖች በመደገፍ ሀገር ወዳድነታችንን በተግባር የምናሳይበት ወቅት ነው " ብለዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያ ካጋጠማት ወቅታዊ ችግር ወጥታ ወደ ተሻለ ምእራፍ እንድትሸጋገር ዳያስፖራው የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበትም ነው የተናገሩት፡፡

ዳያስፖራው የተጎዱ ዜጎችን ከመደገፍ ባለፈ የወደሙ የሕዝብ መገልገያ ተቋማትና መሰረተ ልማቶችን መልሶ በማቋቋም ተሳትፎው ሊጎለብት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይም ዳያስፖራው "ቢያንስ አንድ ቤተሰብ መርዳት አለብኝ" በሚል መርህ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች እገዛ ማድረግ እንዳለበትም አስረድተዋል።

በዚህም በቀጣይ በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን "አንድ ቤተሰብ መርዳት" የሚለውን መርህ ተግባራዊ እንዲያደርጉ የማስተባበር ስራ እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም