በጦርነቱ የተጎዳው ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ የግል ባለኃብቱ ተሳትፎ ሊጎለብት ይገባል

167

ጥር 6/2014/ኢዜአ /በጦርነቱ የተጎዳው ኢኮኖሚ እንዲነቃቃ የግል ባለኃብቱ ተሳትፎ ሊጎለብት እንደሚገባ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሱዋኔ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ ተናገሩ።

መንግሥት የአገሪቱን ሰላም ይበልጥ በማረጋገጥ የተቀዛቀዘውን ኢኮኖሚ ዳግም ለማነቃቃት በርካታ ሥራዎችን  እያከነዋነ መሆኑ ይታወቃል።

በተለይም በአሸባሪው ህወሃት ወረራ የተጎዱ አከባቢዎችን ህዝብን ባሳተፈ መልኩ መልሶ ለመገንባት ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል፡፡

መንግሥት ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚሰራቸው በርካታ ሥራዎችም በግሉ ዘርፍ መደገፍ እንዳለበት ነው በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ሱዋኔ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህሩ ፕሮፌሰር ሙላቱ ፍቃዱ የሚናገሩት።

እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ መንግሥት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፤ ከዛ በመለስ ያሉ ጉዳዮች ላይ ደግሞ የግል ባለኃብቱን ተሳታፊ በማድረግ መስራት አለበት።

በተለይም ደግሞ መንግሥትና የግሉ ባለኃብት በጋራ በመሆን አንዳንድ የልማት ፕሮጀክቶችን በሽርክና  በመንደፍና በማስፈጸምም ሊተባበሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።   

ኢኮኖሚው በአጭር ጊዜ እንዲያንሰራራ የመንግሥትን በጀት ብቻ ከመጠቀም ባለፈ በውጭ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ጋርም በትብብር መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

አቅም ያላቸው የዳያስፖራ አባላት ወደ አገራቸው በመምጣት በተለያዩ የልማት መስኮች ላይ ኢንቨሰት እንዲያደርጉ ጥሪ ሊቀርብላቸው እንደሚገባም ነው የተናገሩት፡፡  

በተለይም በጤናው፣ በትምህርት፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች የተለያዩ ጉዳዮች ላይ በማሳተፍ የልማት እንቅስቃሴዎችን ማፋጠን እንደሚቻል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ልማትና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ለመደገፍ የሚያወጣቸውን ወጪዎች ጥናትን መሰረት ያደረጉና ወጪ ቆጣቢ ሊሆኑ እንደሚገባም ነው የገለጹት፡፡