ዳያስፖራው የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ እውቀቱን ለአገሩ እንዲያበረክት የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ሊጠናከር ይገባል

69

ጥር 06 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራው የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ እውቀቱን ለአገሩ እንዲያበረክት በኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ አሰራር መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ። 

ኢትዮጵያ ለአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ ያቀረበችውን ጥሪ የተቀበሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ወደ አገር ቤት ገብተው ዘርፈ ብዙ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ይገኛሉ።

ኢትዮጵያን በዘላቂ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ለማኖር ዳያስፖራው በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማራ ጥሪ ቀርቦለታል።

"በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የተሻለ የቴክኖሎጂ እውቀትና የፈጠራ ባለቤት ናቸው" ያሉት በደቡብ አፍሪካ በአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ዘርፍ ለ20 ዓመታት በማማከር ስራ የተሰማሩት ዶክተር ትዕግስት ደሱ፤ ከሁለት ወር በፊት ወደ አገራቸው በመምጣት በሙያቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ በአግባቡ የሚሰራበት ባለመሆኑ ዳያስፖራው እውቀቱን ለማካፈል እንደሚቸገር ገልጸው፤ በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ ከተፈለገ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ አሰራር ሊጠናከር ይገባል ሲሉ አመልክተዋል።    

ዳያስፖራው በዘርፉ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ሲያሳይ መንግስት በበኩሉ በአዕምሯዊ ንብረት ላይ ያለውን አሰራር በሕግ በመታገዝ ሊያሻሽል እንደሚገባ ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ መንግስት ከዩኒቨርሲቲዎችና ሌሎች ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመስራት የሚስተዋሉትን ክፍተቶች ሊሞላ ይገባልም ብለዋል።

በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ዘርፍ የሚከወኑ ተግባራት አገሪቷ ቀጣይነት ያለው እድገት እንድታስመዘግብ የሚረዳ ስለመሆኑም ነው ዶክተር ትዕግስት የገለጹት። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም