ሀገራዊ ምክክሩ ልዩነቶችን በመፍታት የሀገር አንድነትን ለማጽናት ያስችላል-ምሁራን

198

እንጅባራ፤ ጥር 5/2014 (ኢዜአ) በቀጣይ የሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት የሀገር አንድነትን ለማጽናት ያስችላል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመላከቱ።


በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ ስሜነህ ቢረስ ለኢዜአ እንደገለጹት ምክክሩ የሀሳብ ልዩነቶችን በማቀራረብ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ያስችላል።

የምክክር መድረኩ አሁን ላይ በየአካባቢው የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን በመፍታትና ግጭቶችን በመቀነስ ህብረተሰቡ ለሀገር ሉዓላዊነትና ለዜጎች ደህንንት መጠበቅ በጋራ እንዲነሱ ያደርጋል ነው ያሉት።

“መድረኩ ለሀገር እድገትና ብልጽግና በጋራ በመሰለፍ በሁሉም ዘርፎች ጠንካራና የበለጸገች ሀገርን ለልጅ ልጆቻችን ለማስረከብ ያስችለናል” ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የህዝብ ወኪሎችና የፖለቲካ ልሂቃኑ ያላቸውን አማራጭ ሀሳብ በማቅረብ የታሰበው ምክክር መድረክ ውጤታማ እንዲሆን የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በዩኒቨርሲቲው የታሪክ ተመራማሪና መምህር ዶክተር አየነው ፋንታ በበኩላቸው በመንግስት የቀረበው ሀገራዊ ምክክር አጀንዳ በተለያየ አግባብ የሚገለጡ የታሪክ ቁርሾዎችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

“ካለፈው ታሪካችን የሚነሱ ያለመግባባት ምንጮችን በማረም ለዛሬው ተግባራችን ትምህርት መውሰድ ይገባል” ነው ያሉት ምሁሩ።

ሀገራዊ ምክክሩን በስኬት ማጠናቀቅ የውስጥ አንድነትን ለማጽናትና የውጭ ሃይሎችን ጫና ለመቀነስ ድርሻው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

በምክክሩ የሚሳተፉ አካላት ከራሳቸው የጥቅም፣ ፍላጎትና ከስሜት በመራቅ ሁሉንም ጉዳዮች ከዘላቂ ሀገራዊና ህዝባዊ ጥቅም አንጻር በመመዘን ለስኬቱ እንዲሰሩ አመልክተዋል።

በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዮች ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር የታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ መንግስትን የሚያስመሰግነው መሆኑን ጠቅሰዋል።

በየደረጃው የሚገኙ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ገለልተኛ በመሆን ለምክክሩ መሳካት የበኩላቸውን ሃላፊነት እንዲወጡ ጠይቀዋል።

የምክክር ሂደቱን ተቋማዊ በማድረግ በዘላቂነት ችግሮችን እየፈቱ ወደ ልዕልና ለመጓዝ እየተደረገ ያለው ጥረት ተገቢና መንግስትን የሚያስመሰግን መሆኑን ምሁራኑ አስታውቀዋል።