የኢንቨስትመንት አማራጮችን የሚያሳየው መረጃ ዳያስፖራው መዋዕለ ነዋዩን በአትራፊ ዘርፍ እንዲያውል ያግዛል

150


አዲስ አበባ፣ ጥር 06/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያሳይ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት መቻሉ ዳያስፖራው መዋዕለ ነዋዩን በአትራፊ ዘርፎች ላይ እንዲያውል እንደሚያግዝ ተገለፀ፡፡

ዳያስፖራው በትክክለኛ መረጃ ላይ ተመስርቶ አትራፊ በሆኑ ዘርፎች መሰማራት የሚያስችለው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ያዘጋጀው የምክክር መድረክና የመስክ ጉብኝት ተከናውኗል።

በጉብኝቱ የተሳተፉት የካሊፎርኒያ ነዋሪው አቶ ብሩክ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት የተዘጋጀው መድረክና ጉብኝቱ በተለያዩ መስኮች ኢንቨስት ማድረግ የሚችልበት አማራጮች እንዳሉት የሚያመላክት ነው።

መርሃ ግብሮቹ ዳያስፖራው ተገቢውን መረጃ እንዲያገኝ ከማስቻላቸው ባሻገር በሁነቱ ላይ መሳተፍ ላልቻሉ ዜግች መረጃ ለማካፈልና የስራ ዕድል ለመፍጠር አቅም እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

ቀደም ሲል መንግስት ዳያስፖራውን ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት የሚቀይሳቸው አሰራሮች መልካም ቢሆኑም የቅንጅት መጓደልና የመረጃ ልውውጥ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የገለጹት ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ የመጡት አቶ ታሪኩ ኑርጋ ናቸው።

ነገር ግን አሁን በዘርፉ ያለውን ቢሮክራሲ የሚያቃልል አሰራር መኖሩን ከምክክር መድረኩ መገንዘባቸውንና የኢንቨስትመንት አማራጮችንም ማየት መቻላቸውን ተናግረዋል።

የኢንዳስትሪ ፓርኮቹ በመሰረተ ልማት የተሟሉና የሰው ኃይሉም በአጭር ጊዜ ሰልጥኖ ወደ ስራ ሊገባ የሚችል መሆኑ ትርፋማና ተወዳዳሪ ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል መረዳታቸውንም ገልጸዋል።

ይህም መዋዕለ ንዋያቸውን በማውጣት ዘርፉን ለመቀላቀል ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው ነው የተናገሩት።

በጉብኝቱ በርካታ እውቀት አግኝተናል የሚሉት የካናዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ኤልሳቤት ሚሊዮንም “የውጭ ሀገር ዜጎች በሀገራችን ተሰማርተው የስራ ዕድል ሲፈጥሩ እኛ ደግሞ ለሀገራችን ምን ማድረግ እንዳለብን እንድናስብ አድርጎናልም” ብለዋል፡፡

መንግስት እውቀትና ገንዘብ ያላቸው ዳያስፖራዎች በቅንጅት እንዲሰሩ ሁኔታዎችን በማመቻቸቱ በአግሮ እንዳስትሪ ዘርፍ ከጓደኞቻቸው ጋር በትብብር ለመስራት መዘጋጀታቸውንም ገልፀዋል።፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ሰለሞን፤ የኢንዱስትሪው መስክ ለብዙ አገራት የእድገታቸው ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ቀልጣፋ በማድረግና መሰረተ ልማቱን በማሟላት ዳያስፖራው እና የአገር ውስጥ ባለሃብቶች ባሉት የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው የመጡ ዳያስፖራዎችም ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ እንዲያዩና እንዲያስተዋውቁ ለማረግ ጉብኝቱና የምክክር መድረኩ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢንቨስትመንት አማራጮችን የተመለከቱት ዳያስፖራዎች በግልም ሆነ በጥምረት ለመስራት መተማመን በውስጣቸው እንደሚያድር እምነታቸውንም ገልጸዋል፡፡