የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ

63

ነቀምቴ፣ ጥር 06/2014 (ኢዜአ) የወለጋ ዩኒቨርሲቲ በግጭት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዳ አያና እና ኪረሙ ወረዳዎች በጊዚያዊ መጠለያ ጣቢያ ለሚገኙ ወገኖች 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚገመት ድጋፍ ማድረጉን አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው የሴቶች፣ የሕፃናትና፣ ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ዶክተር አሊማ ጅብሪል እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን ያደረገው በራሱ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ  ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በማሰባሰብ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ድጋፉን ያሰባሰበው "ዜጎቻችንን እንርዳ’’ በሚል መሪ ሐሳብ በመነሳሳት የድጋፍ አሰባሳቢ በኮሚቴ አዋቅሮ ነው።

ዩኒቨርሲቲው ካደረገው ድጋፍ ውስጥ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብሩን ያሰባሰበው በሀገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር አሊማ እንዳሉት ቀሪው 1 ሚሊየን ብር ደግሞ ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል ከራሱ በጀት ያደረገው ድጋፍ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከ2 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ 181 ኩንታል ሩዝና የዳቦ ዱቄት፣ 4 ኩንታል ጨው፣ 4ሺህ 160 ሊትር የምግብ ዘይት፣ ከ600 በላይ የብርድ ልብስና ፍራሾችን ተፈናቃዮች እንዲደርስ ተጓጉዟል ብለዋል።

ተፈናቃዮቹ በግጭት ምክንያት ከሞቀ ቤታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ ኅብረተሰቡ ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል፡፡

የጊዳ አያና ወረዳ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደረጀ ደበሎ በወረዳው ከ8 ሺህ 800 በላይ ተፈናቃዮች እንዳሉ ገልጸዋል።

ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ የተላከውን የሰብአዊ ድጋፍ ለተፈናቃዮቹ በፍትሃዊነት የሚከፋፈል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኪረሙ ወረዳ የአደጋ ሥጋት ስራ አመራርና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ምትኩ በበኩላቸው ከዩኒቨርሲቲው ለተፈናቃዮች የተላከው አያና ከተማ መድረሱን ገልጸዋል።

በኪረሙ ወረዳም ከ52 ሺህ 350 የሚበልጡ ተፈናቃዮች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም