በአማራና አፋር የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ይሰራል-አገልግሎቱ

87

ላልይበላ ፣ጥር 6/2014 (ኢዜአ) የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት በአማራና አፋር ክልሎች የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ እንደሚሰራ አስታወቀ ።

የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት ሰራተኞች በላልይበላ ከተማ በአሸባሪው ህወሀት ወራሪ ሀይል ውድመት ለደረሰባቸው የጤና ተቋማት የህክምና ቁሳቁሶችን በድጋፍ አበርክተዋል።



የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ በላልይበላ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ርክክብ ስነ-ስርአት ላይ እንዳሉት የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ለህልውና ዘመቻው ስኬታማነት ከ13 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል።


በአሁኑ ወቅትም በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ሀይል በአማራና አፋር ክልሎች ውድመት ለደረሰባቸው ተቋማትና ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች  ከተቋሙ ሰራተኞችና ከአጋር አካላት 28 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ምግብና ቁሳቁስ መሰብሰቡን ገልፀዋል።

ከተሰበሰበው ውስጥ በላልይበላና ሰቆጣ ከተሞች ዘረፋና ውድመት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማትን አገልግሎት ለማስጀመር የሚያግዙ የህክምና ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በከተሞቹ ለጤና ተቋማት 18 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የህሙማን ማስተኛ ፍራሾች፣ ብርድ ልብስ፣ የተለያዩ መድሃኒቶች እንዲሁም የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች በድጋፍ እየቀረቡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በላልይበላ ከተማ ትናንት ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው በዛሬው እለትም በሰቆጣ ከተማ ተመሳሳይ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።


እንደ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለፃ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች  አገልግሎት በአማራና አፋር ክልሎች በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን ለማቃለል ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን የተፈናቀሉ ወገኖች ያሉባቸውን ችግሮች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲያውቀው ለማድረግ ይሰራል።


በሽብር ቡድኑ ወረራ ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ንብረታቸው የወደመባቸውን ዜጎች ወደ ቀደመ ህይወታቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ሊረባረቡ እንደሚገባ አቶ ተስፋሁን አስገንዝበዋል።

የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ በበኩላቸው የሽብር ቡድኑ ወረራ በፈፀመበት ወቅት በከተማዋ በግልና በመንግስት ንብረት ላይ ውድመት ፈፅሟል።

በተለይም የአሸባሪው ወራሪ ሀይል በላልይበላ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ዘረፋ በመፈፀሙ ምክንያት ዜጎችን ለከፋ ማህበራዊ ችግር መጋለጣቸውን አውስተዋል።

የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ሰራተኞችና አጋር አካላት ያደረጉት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በከተማው ጤና ተቋማት የግብዓት እጥረትን  የሚያቃልል መሆኑን አመልክተዋል።

ምክትል ከንቲባው አገልግሎቱ ላደረገው ድጋፍ አመስግነው ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም