የኦሮሚያ ክልል የተፋሰስ ልማት ስራ ለ60 ቀናት ይከናወናል

63

ጥር 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኦሮሚያ የተፋሰስ ልማት ስራ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ለቀጣዮቹ 60 ቀናት እንደሚከናወን ክልሉ አስታወቀ፡፡

በክልል ደረጃ በምዕራብ ሸዋ ዞን ደንዲ ሙሚቻ ቀበሌ የአካባቢው ማኅበረሰብ እንዲሁም ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት የተፋሰስ ልማት ስራ ተከናውኗል።

የዘንድሮው የክልሉ የተፋሰስ ልማት ስራ በወንጪ ሐይቅ ተፋስስ ላይ በማከናወን  በይፋ ተጀምሯል።

መርኃ ግብሩን ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አወሉ አብዲ ናቸው።

የተፋሰስ ስራን ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያብራሩት አቶ አወሉ የአካባቢ ስነ ምህዳርን ከማስጠበቅ ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

የተፈጥሮ ሃብት ልማት በአግባቡ ካልተተገበረ በአገር ደረጃ የተቀመጠውን በምግብ ራስን የመቻል ራዕይ ማሳካት አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአየር ንብረት ለውጥ አማካኝነት በሚከሰት ድርቅ የሚያጋጥመውን ረሃብ ለመከላከል የተፈጥሮ ሃብት ስራና እንክብካቤ ወሳኝ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የተከሰተው ድርቅ የተፈጥሮ ሃብት ስራችንን አጠናክረን እንድንቀጥል አድርጎናልም ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ በበኩላቸው ክልሉ በተፈጥሮ ሃብት የታደለ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን ሃብት በአግባቡ መንከባከብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በክልሉ ከዚህ ቀደም በተሰራው የተፋሰስ ስራ ለውጥ የመጣ ቢሆንም አሁንም ህብረተሰቡ ተግባሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

በተፋሰስ ልማት ስራው ላይ የተሳተፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስራውን በተጠናከረ መልኩ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በደንዲ ወረዳ በወንጪ ሐይቅ ተፋሰስ ዙሪያ በሚሰራው ተፋሰስ ከሀረርጌ አካባቢ የመጡ 100 አርሶ  አደሮች ልምዳቸውን እያካፈሉ ይገኛሉ፡፡

በዘንድሮው የተፋሰስ ስራ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ 6 ሺህ 448 ተፋሰሶችን በመለየት ወደ ተግባር መገባቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ አመላክቷል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም