ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለ ስልጣን ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ አሳሰበ

101

ጥር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ላይ የተገኘው ተደጋጋሚ የኦዲት ግኝት በአስር ቀናት ውስጥ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሶስት አመታት ሳይፈታ በቆየው የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን የኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በመጋበዝ ግምገማ አድርጓል።

የባለስልጣኑን ገቢና ወጪ በተመለከተ ከመንግስት አሰራር ውጭ የሆኑትን በመለየት የፌደራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል።

በኦዲት ግኝቱ የታዩት የአሰራር ግድፈቶች እንዲታረሙ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለባለስልጣኑ ጥያቄ ቢያቀርቡም የእስካሁኑ እርምት አመርቂ አይደለም።

ከ20 በላይ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ያሉበት ባለስልጣኑ ባለቤትነታቸው ያልተረጋገጠና ያለ ጥቅም ለረዥም አመት የተቀመጡ ተሽከርካሪዎች፣ የሚመለከተው አካል ሳይፈቅድ ገንዘብ መሰብሰብ፣ የተሰበሰበውን ገንዘብ ለገንዘብ ሚኒስቴርና ለሚመለከተው አካል ሪፖርት ያለ ማድረግ ይጠቀሳሉ።

ለአንድ ፕሮጀክት የተፈቀደን ገንዘብ ለሌላ ስራ የማዛወር፣ የሲቪል ሰርቪስ አሰራር ከሚፈቅደው ውጭ ለሰራተኞች የትርፍ ጊዜ ክፍያ መፈፀም፣ በወቅቱ ያልተፈፀሙ ውዝፍ ተከፋይ ሂሳብና ሌሎችም ይገኙበታል።

የምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ የኦዲት ግኝቶቹ ለአመታት አስተያየት ሲሰጥባቸው የቆዩና እስካሁን ያልተፈቱ መሆናቸው የተቋሙና እንደ ፍትህ ሚኒስቴር፣ የቱሪዝም ሚኒስቴርና ሌሎች አስፈጻሚ አካላት ድክመት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለስልጣኑን ጨምሮ የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የፍትህ ሚኒስቴርና ሌሎች የኦዲት ግኝቶች ላይ አፋጣኝና ጠንካራ ስራ ሰርተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ሰብሳቢው ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣንና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኦዲት ግኝቶቹ ላይ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ በመውሰድ በአስር ቀናት ውስጥ ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።

በባለስልጣኑ ላይ የተገኙት የኦዲት ግኝቶች ከሙስናና ብልሹ አሰራር ጋር ግንኙነት ያላቸው መሆን አለመሆኑን እንዲያጣራ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ሃላፊነቱን ወስዶ መስራት እንዳለበት ነው አቶ ክርስቲያን የገለጹት።

የኦዲት ግኝቶቹን በተመለከተ የሚመለከታቸው አካላት መርምረው በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ላይ የሚወስዷቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች በአግባቡ መፈፀም አለመፈፀማቸውን እንዲከታተል የፍትህ ሚኒስቴር መታዘዙን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም