በጦርነት የተጎዱ ከተሞችን መልሶ ለመገንባት የተቀናጀ ድጋፍ ያስፈልጋል

98

አዳማ ጥር 04/2014(ኢዜአ) በአፋርና አማራ ክልሎች አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት የተጎዱ ከተሞችን መልሶ ለመገንባት የከተሞች የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ አስገነዘቡ ።

ሚኒስቴሩ በሁለቱ ክልሎች የተጎዱ ከተሞችን መልሶ ለመገንባት ''የቁርጥ ከተሞች እህትማማችነት ጥምረት'' መድረክ በአዳማ ከተማ አካሄዷል ።

ሚኒስትሯ በመድረኩ ላይ እንዳመለከቱት አሸባሪው ቡድን በከፈተው ወረራ በከተሞች ላይ ባደረሰው ጥፋት የመሰረተ ልማት ተቋማት ከጥቅም ውጭ ሆነዋል።

በተለይም ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትና ፋብሪካዎች በዋነኝነት ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ በከተሞቹ የደረሰውን ውድመት በትክክል ለመለየትና የጥፋት ደረጃውን በማጥናት ላይ መሆኑን ወይዘሮ ጫልቱ አስረድተዋል ።

''የወደሙ ከተሞቻችን መልሰን ለመገንባትና ወደ ነበሩበት ከመመለስ ባለፈ በሁሉ አቀፍ ልማት ለማሻገር የሁሉም ጥምረትና ርብርብ የሚያስፈልገን ጊዜ አሁን ነው'' ብለዋል ።

መድረኩ በአፋርና አማራ ክልሎች በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ከተሞች መሠረተ ልማት በተቀናጀ መልኩ መልሶ ለመገንባት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ሚኒስትሯ ተናግረው የወደሙ የመሠረተ ልማት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ሁሉም ድርሻውን ወስዶ ወደ ሥራ የሚገባበት እንደሚሆን አስረድተዋል ።

በሚኒስቴሩ የከተሞች መልካም አስተዳደርና አቅም ግንባታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ ጥምረቱ በዋነኝነት በአማራና በአፋር ክልሎች መልሶ ግንባታ ላይ የሚያተኩር ቢሆንም፤በቤኒሻንጉል ጉምዝና በኦሮሚያ ክልሎች በሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ሃይሎች ጥፋት የደረሰባቸውን ከተሞች እንደሚመለከት ገልጸዋል።

''ለወደሙ ከተሞቻችን መልሶ ግንባታ ያለን ቁርጠኝነት የሚለካው ተጋግዘንና እርስ በራሳችን ተደጋግፈን ከገጠመን ሀገራዊ ችግር መውጣት ስንችል ነው''ያሉት ሃላፊው "የተግባር አንድነት፣ አብሮነትና የህዝቦች ወንድማማችነት በዘላቂነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል" ብለዋል ።

"ጉዳት የደረሰባቸው ከተሞች ዝርዝር ፣ የደረሰ ጉዳት ዓይነት፣ መጠንና ስፋት ተለይቶ ይቀርባል" ያሉት አቶ ብርሃኑ ድጋፍ የሚያደርጉ ከተሞች የሚደግፉትን ከተሞች በመምረጥ ከቢሮ ቁሳቁስ ጀምሮ ዝርዝር ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም