በኦሮሚያ ክልል ከነገ ጀምሮ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ መርሃ ግብሮች ተዘጋጅተዋል

89

ጥር 4/2014/ኢዜአ/ በኦሮሚያ ክልል ዳያስፖራዎች የሚሳተፉባቸው የተለያዩ መርሃ ግብሮች ከነገ ጀምሮ የሚካሄዱ መሆኑን የዳያስፖራ አቀባበል ኮሚቴው አስታወቀ።

በወጣው መርሃ ግብር መሰረት በነገው እለት (ጥር 5 ቀን 2014 ዓ.ም) የኦሮሚያ እንቨስትመንት ኮሚሽን ከዳያፖራው ጋር በክልሉ ባለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ላይ ይመክራል።

የውይይቱ ዋና ጉዳይ ዳያስፖራው በክልሉ ባሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት እንዲሳተፍ ለማስቻል መሆኑን የኦሮሚያ ዳያስፖራ ጉዳዮች ዳይሬክተር እና የክልሉ ፕሬዝዳንት አማካሪ አቶ አሚን ጁንዲ ገልጸዋል።

በመቀጠለም በመጭው ቅዳሜ በአዳማ ዳያስፖራዎች የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር ይካሄዳል ተብሏል።

በዚሁ እለት የክልሉ ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የስራ የኃላፊዎች ተገኝተው ዳያስፖራዎችን እንኳን ደህና መጣችሁ የሚሉ ይሆናል።

በክልሉ የተለያዩ የኢንቨስትመንትና የልማት ስራዎች የሚጎበኙ መሆኑም ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሰዓዳ ዑስማን፤ ዳያስፖራዎች በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ የቱሪስት ስፍራዎችን እንደሚጎበኙ ገልጸዋል።

የወንጪ ሃይቅ፣ ጂማ ከተማ፣ የባሌ ተራራዎችና ሌሎች የቱሪስት መስህቦች ይጎበኛሉ ብለዋል።

በአዳማ ከተማ ዳያስፖራውን ጨምሮ 30 ሺህ ሰዎች የሚሳተፉበት የሩጫ ውድድር እንደሚካሄድ የብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን ዋና አስልጣኝ ኮማንደር ሁሴን ሼቦ ገልጸዋል።

በውድድሩ ከ500 በላይ ታዋቂ አትሌቶች የሚሳተፉበት ሲሆን እስከ 10ኛ ለሚወጡ ተወዳዳሪዎች እንደየደረጃቸው ሽልማት ተዘጋጅቷል ብለዋል።

ዳያስፖራው ከከተማ ውጭ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች ላይ ምቹ ትራንስፖርት መዘጋጀቱን ገልጸው ስለ ፕሮግራሞቹ ተጨማሪ ማብራሪያ በ https://forms.gle/Qacdz1xweiYNEu9z9 ይገለፃል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም