ኢትዮጵያና ሲንጋፖር በንግድና ኢንቨስትመንት በጋራ ለመስራት ተስማሙ

98
ሲንጋፖር ነሃሴ 22/2010 ኢትዮጵያና ሲንጋፖር በመካከላቸው ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በጋራ ለመስራት ተስማሙ። አገራቱ ስምምነት ላይ የደረሱት በየሁለት ዓመቱ ሲንጋፖር በሚካሄደው የሲንጋፖርና ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች የሚኒስትሮች የልምድ ልውውጥ ጉብኝት ጎን ለጎን የሁለቱ አገራት ባለስልጣናት ባደረጉት ውይይት ነው። በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል ከሲንጋፖር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቪቪያን ባላክሪሽናናን ጋር በሁለትዮሽ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች የተወያዩ ሲሆን ግንኙነቱን ይበልጥ ለማጠናከርም ተስማምተዋል። ኢትዮጵያና ሲንጋፖር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጎልበት ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የላከው መግለጫ ጠቁሟል። ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ12 የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት ይልምድ ልውውጡ የተከናወነው ነሐሴ 21 እና 22 ቀን 2010 ዓ.ም ነው። የውጭ ጉዳይ ሚኒስተር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል በቆይታቸው በሲንጋፖር የሚገኘውን የቴክኒክ ትምህርት ኢንስቲትዩት ጎብኝተዋል።   አገራቱ በአየር ትራንስፖርት አገልግሎት፣ ተደራራቢ የታክስ ስርዓትን በማስወገድና በሌሎች የጋራ ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ላይ አብሮ ለመስራት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል።   ሲንጋፖር ኢትዮጵያን ጨምሮ 50 በሚሆኑ የአፍሪካ አገራት መካከል ያለውን የንግድ፣ ቱሪዝምና የኢንቨስትመንት ግንኙነትን ለማጠናከር እየሰራች ነው፤ ከ60 በላይ ኩባንያዎቿም ከ50 በላይ በሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት በኢንቨስትመንት ዘርፎች መሰማራተቸውም ለዚህ ማሳያ ነው።   እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2015 በሲንጋፖርና አፍሪካ መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት 11 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር መድረሱንም መረጃዎች ያሳያሉ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም