የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለጭነት ቅድሚያ ቦታ ማስያዝ የሚያስችል አሰራር ጀመረ

94

አዲስ አበባ፣ ጥር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የካርጎ እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ደንበኞች ለሚያስጭኑት ዕቃ በቅድሚያ ቦታ ማስያዝ የሚያስችል አዲስ አሰራር ጀመረ።

አሰራሩ ደንበኞች የበረራ መርሃ ግብሮችን ለማረጋገጥ፣ የቦታ መኖርን፣ የመጫን አቅምን እንዲሁም በነጠላ እና በሚመች መንገድ ጭነትን ወዲያው ቦታ ማስያዝ የሚያስችል መሆኑን ተገልጿል።

ደንበኞች cargobooking.ethiopianairlines.com በሚለው መተግበሪያ በመግባት የተገለጹትን አገልግሎቶች እንዲያረጋግጡ ያስችላቸዋል ነው የተባለው።

የአየር መንገዱ ካርጎ እና ሎጅስቲክስ አገልግሎት የደንበኞቹን አጠቃቀም ለማሳደግ የሚያስችል የሞባይል መተግበሪያ በመጀመር ደንበኞች ቅድሚያ ቦታ እንዲይዙ እያደረገ መሆኑን የሚታወቅ ነው።

በአንድሮይድ እና በአይ.ኦ.ኤስ የሚገኘው ይኸው የሞባይል መተግበሪያ ለደንበኞች አመቺ ከመሆኑም ባለፈ ደንበኞች ራሳቸው ጊዜውን የጠበቀ ማሻሻያ ሊያደርጉበት የሚችል እንደሆነም ተገልጿል።

በዚህም ደንበኞች የበረራ መርሃ ግብርን ማረጋገጥ፣ ጥያቄ ማቅረብ፣ ጭነቱ ዝግጁ ሲሆን ማሳወቂያዎችን መቀበል፣ የቻርተር በረራዎችን መያዝ እና ጭነቶችን መከታተል የሚችሉ ይሆናል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አሥፈፃሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም “ለጭነት ቦታ ማስመዝገቢያ አጠቃቀም ለደንበኞቻችን ስናቀርብ ደስታ ይሰማናል” ብለዋል።

የሎጂስቲክስ እሴት ሰንሰለትን ዲጂታል በማድረግ መላው የአየር ጭነት ሂደትን ከወረቀት አሰራር ለማላቀቅ አየር መንገዱ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ሂደቱን ከወረቀት አሰራር ማላቀቅ ለደንበኞች ምቹ እና ከግድፈት የፀዳ አገልግሎት የሚያስገኝ ብቻ ሳይሆን ይበልጥ ቀልጣፋ አሰራር የሚፈጥርና የአየር መንገዱን ዘላቂ ግቦችን ለማሳካት የሚረዳ ነው ብለዋል።

የኦንላይን ቦታ ማስያዣ አሰራሩ የጭነት ደንበኞች እና አስተላላፊዎችን የአየር መንገዱን አስተማማኝ የጭነት አገልግሎት በቀላሉ የመጠቀም አቅማቸውን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን ዋና ሥራ አሥፈፃሚው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሙሉ በሙሉ ዘመናዊ በሆነ እና በአዳዲስ ቴክኖሎጂ የታገዘ የካርጎ አገልግሎት በመስጠት ከአፍሪካ ቀዳሚ አየር መንገድ ነው።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ

‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም