አርቲስት ዓለምጸሃይ ወዳጆን ጨምሮ ለሌሎች አንጋፋ የኢትዮጵያ አርቲስቶች በብሔራዊ ትያትር ቤት ደማቅ አቀባበል ተደረገ

3133

አዲስ አበባ ነሃሴ 22/2010 አርቲስት ዓለምጸሃይ ወዳጆን ጨምሮ ለሌሎች አንጋፋ የኢትዮጵያ አርቲስቶች በብሔራዊ ትያትር ቤት ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው።

ከአንጋፋ አርቲስቶች መካከል አርቲስት ተክሌ ደስታና አበበ በለው ይገኙበታል፡፡

አርቲስት ዓለምጸሃይ ከ27 ዓመታት የስደት ቆይታ በኋላ ዛሬ ጠዋት ወደ አገሯ መግባቷን አስመልክቶ በብሔራዊ ትያትር ቤት አንጋፋ የኪነ ጥበብ የሙያ አጋሮቿ በተገኙበት ደማቅ አቀባበል ተደርጓል።

በአቀባበል ስነስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን አርቲስቷ በስደት በምትኖርበት አገረ አሜሪካ የባህል አምባሳደር ሆና እየሰራች መቆየቷን ገልጸዋል።

እጅግ በበርካታ ስራዎቿ የምትታወቀው አርቲስት ዓለምጸሃይ በኖረችበት አገር ኢትዮጵያውያን ስለ ታሪካቸው እንዲያውቁ የባህል አምባሳደር ሆና ማገልገሏን ተናግረዋል።

ስለሆነም አርቲስቷ የመንግስትን ጥሪ በመቀበል በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ወደ አገሯ በመግባቷ ”እንኳን ደህና መጣሽ፣ እኳን ከህዝብሽ ጋር ተቀላቀልሽ” ብለዋታል።

አርቲስት ዓለምጸሃይ ወዳጆ በስደት ህይወት ቤተሰቧን ለማስተዳደር እየሰራች መሆኑን ጠቅሳ ለሙያው ባላት ፍቅር ከሙያዋ ሳትለይ በተዋናይነት፣ በገጣሚነትና በተያያዥ የኪነ ጥበብ ስራዎች ማሳለፏን ትናገራለች።

አርቲስቷ በአሜሪካን አገር የጣይቱ የባህል ማዕከል መስራች፣ የአማርኛ ቤተ መጽሃፍት የመሰረተችና የተለያዩ የኪነ ጥበብ ስልጠናዎችን ስትሰጥ መቆየቷንም ገልፃለች።

የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ሙያቸውን ተጠቅመው ለእኩልነት፣ ለፍትህና ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡ ስራዎች ላይ እንዲያተኩሩ ጥሪ አቅርባለች።

በተጨማሪም ያደጉ አገሮች አሁን ያሉበት የስልጣኔ ደረጃ ላይ የደረሱት የህዝባቸውን አስተሳሰብ በተሻለ መልኩ መለወጥ ስለቻሉ በመሆኑ ለአስተሳሰብ ለውጥ መስራት እንደሚያስፈልግ ገልጻለች።

ከሙያ አጋሮቿ መካከል አርቲስት ደበበ እሸቱ በሰጠው ምስክርነት ”ዓለምጸሃይ ብርቱ ከራሷ ጥቅም ይልቅ ለሌሎች የምትጨነቅ ሩህሩህ ሰው ናት” ብሏል።

በአቀባበል ዝግጅቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ የአርቲስቷ የረጅም ጊዜ ህልም የነበረው የእቴጌ ጣይቱን ሃውልት ኢትዮጵያ ውስጥ የመትከል ህልም ለማሳካት አስተዳደሩ እገዛ የሚያደርግላት እንደሆነ ጠቁመዋል።

አርቲስቷ በኢትዮጰያ ቆይታዋ በየትያትር ቤቱ ልምዷን እንድታካፍል እንዲሁም በዩኒቨርሲቲዎች በስነ-ጥበብ ዙሪያ ስልጠና እንድትሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለምጸሀይ በ18 ዓመቷ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ በብሔራዊ ትያትር ለሁለት ዓመታት የተሰጠውን ስልጠና በመከታተል በዚያው ትያትር ቤት በከፍተኛ ተዋናይነት ተቀጥራ ለ17 አመታት በተዋናይነትና በጸሃፊነት አገልግላለች።

በዚህ ጊዜ ውስጥ በተዋናይነት በቬኑሱ ነጋዴ፣ ሐምሌትና ዋናው ተቆጣጣሪ በተሰኙ ከውጭ ቋንቋ ተተርጉመው በተዘጋጁ ትያትሮች ላይ በመተወን ከፍተኛ የሆነ ተወዳጅነትን ያተረፈች አርቲስት ናት።

የኢትዮጵያ ተዋናዮችን ማህበር መስራች አባል ከመሆን ባለፈም በምክትል ሊቀመንበርነት ለ14 ዓመታት በማገልገል የተዋናዮች ደመወዝ እንዲሻሻል ስኬታማ ቅስቀሳ ማድረግ ችላለች።

‘በሩ’ በሚል ርዕስ የጻፈችው ትያትር በራስ ቲያትር እየታየ በነበረበት ጊዜ መንግስትን የሚተች ዓይነት በመሆኑ አንዳንድ ማሻሻያዎችን እንድታደርግበት በማስታወቂያ ሚኒስትሩ በኩል ትዕዛዝ ተሰጥቷት ባለመቀበሏ ትያትሩ እንዳይታይ ታግዷል።

በ1992 ዓ ም ጣይቱ የባህል ማዕከልን በዋሽንግተን ዲሲ ማቋቋም መቻሏ የኪነጥበብ ስራዋን በስፋት ለመስራት ዕድል ማግኘቷን ትናገራለች።