በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር መሳተፋችን የአብሮነት እሴቶችን ለመገንባት አግዞናል-ወጣቶች

59

ጎንደር ፤ጥር 3/2014 (ኢዜአ) በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር መሳተፋቸው ዘመን ተሻጋሪ የአብሮነት እሴቶችን ለመገንባት እንዳገዛቸው በጎንደር ከተማ በብሔራዊ በጎ ፈቃድ መርሃ ግብር የተሳተፉ ወጣቶች ገለጹ፡፡

በጎንደር ከተማ በሰላም ሚኒስቴር አስተባባሪነት ለ10 ተከታታይ ወራት በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር  ሲሳተፉ ለቆዩ ወጣቶች የሽኝት መርሃ ግብር  ዛሬ ተካሄዷል።  

በመርሃ ግብሩ የኢትዮጵያውያንን የእንግዳ ተቀባይነት፣ አክባሪነትና በዘመናት የተገነቡት የአብሮነት እሴቶች  ማረጋገጥ መቻሉን ከደቡብ ክልል በመርሃ ግብሩ የተሳተፈው ወጣት አሸናፊ ሙላት ገልጿል።

''በጎንደር ቆይታዬ ህዝቡ እንደ ቤተሰብና እንደ ወላጅ ያደረገልኝ እንክብካቤና ወገናዊ ፍቅር የህዝቡን የአብሮነት እሴቶች እኛ ወጣቶች በትውልድ ቅብብሎሽ ለማስቀጠል ኃላፊነት እንዳለብን የተገነዘብኩበት ነው'' ብሏል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል የመጣችው ወጣት አብዮት በየነ በበኩሏ ባለፉት 10 ወራት ከከተማው ህዝብ ጋር ጥብቅ የአብሮነትና የቤተሰብ ግንኙነት ለመመስረት መቻሏን ገልፃለች።

ወደ መጣችበት አካባቢ እንደተመለሰች ይህን የአብሮነት እሴቶች ለማስቀጠል በትኩረት እንደምትሰራ ገልጻ፣ የህዝቡ ባህል፣ እምነትና በጎ ምግባሮች የህወይት ክህሎቷን ለማጎልበት እንዳገዛት ተናግራለች።  

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ  የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩ ተሳታፊ ወጣቶች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር የጎላ ሚና እንደሚኖራቸው አመልክተዋል።

መልካም በማሰብና በጎ ተግባራትን በማከናወን በሀገር ሰላም ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ወጣቶቹ ባለፉት 10 ወራት በከተማው ውስጥ የአቅመ ደካሞችን  መኖሪያ ቤት በመጠገን፣ የማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ በችግኝ ተከላ፣ በጽዳትና ውበት ማህበራዊ አገልግሎቶች ማበርከታቸው ተገልጿል።

የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩ ለተሳተፉት 116 ወጣቶች በከተማ አስተዳዳሩ የእውቅና የምስክር ወረቀት መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም